ተማሪዋን አስገድዶ የደፈረው የተማሪዎች ዲን በነጻ ተለቀቀ

ታህሳስ  ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የጎንደር ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ዲን የሆኑት አቶ ናትናኤል ህዳር 27 ቀን 2005 ዓም የሚያስተምሯትን ተማሪ ስልክ በመደወል ከምሽቱ 1፡30 ገዳማ ቢሯቸው ድረስ ካስጠሩ በኋላ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደፈጸሙባት መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ተማሪዎች እንደገለጹት ደግሞ የጸጥታ አካላት እንዲሁም የዩኒቨርስቲው ባለስልጣናት ለፖሊስ ሊተባባሩ ባለመቻላቸው የተማሪዋ ህይወት አደጋ ውስጥ ወድቋል።

የተደፈረችው ተማሪ በግሏ ጥረት ወደ ዩኒቨርስቲው ሆስፒታል በመሄድ አስፈላጊውን የህክምና ምርመራ ያደረገች ሲሆን የምርመራው ውጤትም ተማሪዋ የአስገድዶ መደፈር ሰላባ መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው።

ተማሪዋን አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ ያለውን የኃላፊነት ቦታ እንዲሁም የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑ ወዳጆቹን በመጠቀም የምርመራ ውጤቱን ማስረጃ ከዩኒቨርስቲ ሆስፒታሉ ደብዛውን ለማጥፋት ቢሞክርም ተጠቂዋ የህክምና ምርመራ ውጤቷን አስቀድማ በመውሰዷ ሳይሳካለት መቅረቱን መዘገባችን ይታወሳል። ይህም ሆኖ ግን የዩኒቨርስቲው ባለስልጣናት ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ እየሞከሩ መሆኑ ታውቋል። በዩኒቨርስቲው አቋም የተበሳጩት ሌሎች ሴት ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን በማለት እያንገራገሩ ነው።

አንንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተል ተማሪ እንደገለጸው የተደፈረችው ተማሪ የእስልምና እምነት ተከታይ በመሆኑዋ ጉዳዩ ሀይማኖታዊ ገጽታ እንዳይሰጠው በመፍራት ለመሸፋፋን እየተሞኮረ ነው። ኢሳት በተማሪው የቀረበውን አስተያየት ለማጣራት ሙከራ እያደረገ ነው።

የተደፈረችው ተማሪ የህክምና ውጤቱን ማስረጃ በመያዝ ታህሳስ 12 ቀን 2005 ዓም ለጎንደር ከተማ አስተዳደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ያመለከተች ቢሆንም ፖሊስ መረጃውን ተቀብሎ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወስድ የቆየ ሲሆን የተጠቂዋ ተማሪ ቤተሰቦችና አንዳንድ መምህራን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት እና ጫና ታህሳስ 20 ቀን 2005 ዓ,ም ከቀኑ 9፡00 ገዳማ ተጠርጣሪው አቶ ናትናኤል በፖሊስ ተይዘው እንዲታሰሩ መደረጉ ይታወሳል።

የልጆቿን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ ግለሰቦችም ደፍሯል የተባለው ግለሰብ ያለውን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና መንግስታዊ ስልጣን ተጠቅሞ ወንጀሉን በቀላሉ እንዲጠፋ ሊያስደርግ ይችላል የሚለው ስጋት እውን እየሆነ መምጣቱን ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ተማሪ ተናግሯል።

አስገድዶ ደፍሯል የተባለው   አቶ ናትናኤል ልጅና ሚስት ያለው ሲሆን ወደ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ከመግባቱ በፊት በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ በወረዳ ካቢኔነት ሰርቷል።

ለገዢው ፓርቲ ባለው ታማኝነትና አገልጋይነት በቀላሉ የዩኒቨርስቲ መምህር መሆን የቻለ ሲሆን ግለሰቡ ለገዢው ፓርቲ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በሚሰራው የፖለቲካ ስራ ያለ ትምህርት ዝግጅት እና ያለ ብቃቱ የተማሪዎች ዲን መሆን እንደቻለ የዩኒቨርስቲው ሰራተኞች ይገልጻሉ።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ ውስጥ በዩኒቨርስቲው አመራሮች የሚፈጸመው ሙስና ከልክ እያለፈ መምጣቱን የግቢው ሰራተኞች ይናገራሉ።