ተመድ በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣል በቀረበ ሃሳብ ላይ አርብ ድምፅ እንደሚሰጥ ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 14 ፥ 2009)

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣል በቀረበ ሃሳብ ላይ አርብ ድምፅ እንደሚሰጥ ተገለጸ።

በአሜሪካ የቀረበው ይኸው ሃሳብ በፈረንሳይና በብሪታኒያ መንግስታት በኩል ድጋፍን ቢያገኝም በምክር ቤቱ ድምፅን በድምፅ የመጣል መብት ባላቸው ቻይንናና ሩሲያ በኩል ድጋፍን አያገኝም ተብሎ ተሰግቷል።

አሜሪካ በሃገሪቱ ላይ እንዲጣል የምትፈልገው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በሃገሪቱ ያለውን ግጭት ዕልባት ለመስጠት ያግዛል ስትል ሌሎች ሃገራት በበኩላቸው ዕርምጃው መፍትሄን የሚያመጣ አይደለም ሲሉ ተቃውሞን እያቀረቡ ይገኛል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የደቡብ ሱዳን መንግስትና አማጺ ቡድን ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ሙከራ ቢያደርጉም ሁለቱ ወገኖች የደረሱትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ሳያደርጉ ዳግም ወደ ግጭት መግባታቸው ይታወሳል።

በፕሬዚደንት ሳል ባኪርና በሪክ ማቻር አማጺ ቡድን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ የአማጺ ቡድኑ መሪና የምክትል ፕሬዚደንት ስልጣንን ተረክበው የነበሩት ሪክ ማቻር ከሃገሪቱ ኮብልለው በደቡብ አፍሪካ ይገኛሉ።

አሜሪካን እና ምዕራባዊያን ሃገራት ሁለቱ ወገኖች የደረሱትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥረት ቢያደርጉም ምንም ውጤት ሊያመጣ አለመቻሉን የፖለቲካ ተንታኞች አስታውቀዋል።

አሜሪካ በበኩሏ በአዲሲቷ ሃገር ደቡብ ሱዳን ያለውን ግጭት ዕልባት ለመስጠት በሃገሪቱ ላይ የመሳሪያ ማዕቀብ መጣሉ መፍትሄን እንደሚያመጣ ትገልጻለች።

በዚሁ ሃሳብ ላይ ውሳኔን ለማስተላለፍ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት አርብ ድምፅን ይሰጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ለምክር ቤቱ የቀረበውን ሃሳብ እንደሚቃወሙት ከወዲሁ ይፋ አድርገዋል።

ተሰናባቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን በሃገሪቱ ላይ አፋጣኝ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ካልተጣለ በደቡብ ሱዳን የዘር ማጥፋት ድርጊቱ ሊፈጸም ይችላል ሲሉ በተያዘው ሳምንት ማሳሰባቸው ይታወሳል።

በሃገሪቱ የሚታተም ጋዜጣ ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ የተለያዩ  የጦር መሳሪያዎችን ለመግዛት ያደረገችውን ሚስጢራዊ ሰነድ ዋቢ ባማድረግ ከወራት በፊት ዘገባን እንዳቀረበ መዘገባችን የሚታወስ ነው።