ተመድ በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ ችግር እያሳሰበኝ ነው አለ

ኢሳት (መስከረም 27 ፥ 2009)

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ ችግር እያሳሰበው መሆኑን ገለጸ።

የኮሚሽኑ ቃል-አቀባይ ሪፖርት ኮልቪል ከጄኔቫ እንደገለጹት በእሬቻ በዓል ላይ ባለፈው ሳምንት የተፈጸመውን እልቂት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል እና በደቡብ ምስራቅ አዲስ አበባ ያለው የጸጥታ ችግር እየተባባሰ መጥቷል።

በተለይም በቢሾፍቱ እሬቻ በዓል ላይ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር በውል አለመታወቁ እና በመንግስት ላይ እምነት መታጣቱ የጸጥታ ችግሩን እንዳባባሰው ቃለአቀባዩ አስታውቀዋል።

በዚሁም ምክንያት ጉዳዩን የሚያጣራ አካል መሰየም እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እምነቱ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ማናቸውም ወገኖች ተጠያቄ መሆን እንዳለባቸው የኮሚሽኑ ቃለ-አቀባይ አሳሰበዋል።

በቢሾፍቱ በእሪቻ በዓል ላይ የተቀሰቀሰውን ሰላማዊ ተቃውሞ ለማብረድ በሚል በስፍራው የተመደቡ የአጋዚ ጦር አባላትና የፌዴራል ፖሊስ ታጣቂዎች አስለቃሽ ጭስና ጥይት በመተኮሳቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ ጋር ተያይዞ መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።