ኢሳት (የካቲት 16 ፥ 2009)
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሶማሌ ክልል በመባባስ ላይ ያለውን የከፋ የድርቅ አደጋ ለመታደግ የመደበውን የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ተከትሎ መንግስት ከመጠባቂያ ምግብ ክምችት የእርዳታ አቅርቦት ወደ ስፍራው እንዲጓጓዝ ማድረጉን አስታወቀ።
በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ከፍተኛ ጉዳትን እያደረሰ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ የሰው ህይወት ሊያጠፋ ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩንም የእርዳታ ተቋማት ገልጸዋል።
በሶማሌ ክልል የሚገኙ ዘጠኝ ዞኖች አስከፊ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ በመግለጽ ላይ ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም አቀፍ ማህበረሰብ አፋጣኝ ርብርብ እንዲያደርግ አሳስቧል።
ድርጅቱ ማክሰኞ ለአስቸኳይ ጊዜ የሚውል ድጋፍ ከያዘው በጀት ውስጥ 18 ሚሊዮን ዶላር ለዚሁ ተግባር እንዲውል መወሰኑን ከስዊዘርላንድ ማስታወቁ ይታወሳል። የገንዘብ ድጋፍ ይፋ መደረገን ተከትሎ መንግስት ወደ 141 ሺ ሜትሪክ ቶን እህል ከመጠባበቂያ ምግብ ክምችትን በማውጣት ወደ ስፍራው እያጓጓዘ መሆኑን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
በዘጠኝ ዞኖች ውስጥ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መንግስት አፋጣኝ የእርዳታ አቅርቦት እንዲያደርግላቸው ሲጠይቁ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በእርዳታ አቅርቦት መዘግየት በሰው ህይወት ላይ አደጋ እንዳይደርስ ስጋት መፍጠሩንም የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
በተለይ በሶማሌ ክልል የሚካሄደው የምግብ አቅርቦት የህይወት ማዳን ተልዕኮ እንዳለው አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንዲለቀቅ የወሰነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
በዚሁ የገንዘብ ልገሳ የአለም ምግብር ፕሮርግራም ከመንግስትና ከተለያዩ የዕርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የከፋ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ሰዎች የሰብዓዊ ስራን እንዲያከናውኑ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ከአሁን በኋላ የሚፈጠር የእርዳታ አቅርቦትን መዘግየት የሰው ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም በድርጅቱ የእርዳታ ማስተባበሪያ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ስቴፋን ኦ-ብግሪያን መናገራቸው UN-News ዘግቧል።
የአርብቶ አደሮች የቁም እንስሳት በምግብ እጥረት እንዳይሞቱ ሲባል እንስሶቹ ለዩኒቨርስቲዎችና ለሌሎች ተቋማት በምግብነት እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድርቁ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።