ተመድና የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ ለምግብ እርዳታ ገቢ የማሰባሰብ ዘመቻ ጀመሩ

 

ኢሳት (ሚያዚያ 19 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ሰዎች የሚያስፈልገው ድጋፍ በበቂ ሁኔታ አለመገኘቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና መንግስት በለጋሽ ሃገራት በመዘዋወር ገቢ የማሰባሰብ ዘመቻ ጀመሩ።

ይኸው ማክሰኞ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ ከተማ የተጀመረው ድጋፍን የማሰባሰብ ዘመቻው በስዊዘርላንድ ጄኔቫና በዚህ በአሜሪካ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መቀመጫ በሆነችው የኒውዮርክ ከተማ እንደሚካሄድም ታውቋል።

ከ10 ሚሊዮን ለሚበልጡ ተረጂዎች ወደ 1.4 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ቢያስፈልግም፣ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት መኖሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።

የድጋፉ በበቂ ሁኔታ አለመገኘትን ተከትሎም መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተባበሩት መንግስታት ተወካዮችና የእርዳታ ተቋማት ከመንግስት ጋር በመተባበር የእርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻውን እንደጀመሩ ለመረዳት ተችሏል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮግራም ተወካይ እንዲሁም የድርጅቱ የስደተኞች ኮሚሽን ሃላፊዎችና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ተቋማት አስተባባሪ ሃላፊዎች በዚህ አለም አቀፍ የድጋፍ ማሰባሰብ ጉዞ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኝም ታውቋል።

ከመንግስት በኩልም የብሄራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን የሆኑት አቶ ምትኩ ካሳ በዘመቻው የተካተቱ ሲሆን ተቋማቱ ለተረጂዎች የሚሆን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን ለማሰባሰብ እቅድ መያዛቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።

እነዚህ ድርጅቶች ከአንድ ወር በፊት ለ90 ቀን የሚቆይ የእርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻን በአለም አቀፍ ደረጃ ጀምረው የነበረ ቢሆንም እንቅስቃሴያቸው የሃገሪቱን ገጽታ የሚያበላሽ ነው ተብሎ በመንግስት እንዲቀር መደረጉን ምንጮት ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።

ይኸው በአዲስ መልክ የተጀመረው አለም አቀፍ ዘመቻ ለመጀመሪያ ጊዜ መንግስትን ተሳታፊ በማድረግ እየተካሄደ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።

አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በተለይ በሶማሊ እና አፋር ክልሎች በነዋሪዎች ላይ ክፉኛ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ወደ 10.2 ሚሊዮን ሰዎችም ለእለት የሚሆን በቂ የምግብ ድጋፍን እያገኙ እንዳልሆን በመግለጽ ላይ ናቸው።