ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2008)
በ1977 በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት የሮክ ሙዚቃ ኮንሰርት በማዘጋጀት 65 ሚሊዮን ዶላር የዕርዳታ ገንዘብ በመሰብሰብ ለድርቅ ተጠቂዎች የለገሰው አየርላንዳዊው የሙዚቃ አቀንቃኝ ቦብ ጌልዶች ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ተበረከተለት።
“ላይቭ ኤይድ” የሚል የሙዚቃ ድግስ ከማዘጋጀቱ ቀደም ብሎ በዝግጅቱ “የገና በዓል መሆኑን ያውቁ ይሆን? (Do they know it is Christmas?) የተሰኘ ነጠላ ዜማ በመስራት እኤአ በ1984 የገና በዓል ቀደም ብሎ ለገበያ በማዋል ይገኛል ተብሎ ከተጠበቀው 70ሺ የእግሊዝ ፓውንድ በላይ 8 ሚሊዮን ፓውንድ በኢትዮጵያ ለተከሰተው ድርቅ ሰብስቧል።
ከዚያም በእንግሊዙ ዌምብሌይ እና በአሜርካ ፊላዴልፊያ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ስታዲየም የሙዚቃ ድግሱን በማዘጋጀት የእርዳታ ገንዘብ አሰባስቧል። የሙዚቃ ዝግጅቶቹን በዓለም ያሉ 1.5 ቢሊዮን ህዝብ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ተከታትሎታል።
ቦብ ጌልዶፍ በወቅቱ ላበረከተው ሰብዓዊ ተግባርና፣ በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ጋር የልማት ኢንቨስትመንት ላይ እየተሳተፈ ነው በሚል የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቶታል። የክብር ዶክትሬቱን ከዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ክንደያ ገብረህይወት መቀበሉም ተገልጿል።
በ ላይብ ኤይድ ዝግጅት የተሰበሰበው ገንዘብ ለኢትዮጵያውያን ሲሰጥ በወቅቱ ድርቁ ባጠቃው የትግራይ ክ/ሃገር አካባቢውን ተቆጣጥሮ ለነበረው የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሃት) ተሰጥቶ ገንዘቡ ለድርቅ ተጠቂው ከማዋል ይልቅ በኢትዮጵያ መንግስት ወንበዴዎች ተብለው ለሚጠሩት አማጽያን የጦር መሳሪያ መግዣ መዋሉን የህወሃት የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ አቶ ገብረመድህን አርአያ እና የኢኮኖሚ ክፍል የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርኸ መናገራቸው ይታወሳል።
ቢቢሲ ተመሳሳይ መረጃ አውጥቶ ቦብ ጌልዶፍ ቢያስተባብልም ከተገኘው የእርዳታ ውስጥ 20 በመቶው አማጺያኑ ተቆጣጥረውት ለነበረው አካባቢ መዋሉን አምኗል።
አማጽያኑ ሃገሪቷን ከተቆጣጠሩ በኋላ ቦብ ጌልዶፍ ከህወሃት መንግስት ጋር በቅርብ ከመስራት ባለፈ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርቷል።
የቦብ ጌልዶፍ 8 ማይል የተባለ ድርጅት 200 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት በአዋሽ አክሲዮን ማህበር ኢንቨስት አድርጓል ፥ እንዲሁም ከቀድሞ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ የኢኮኖሚ ባለሙያዋ እሌኒ ገብረመድህን ጋር በመሆን በእርሻና ፋይናንስ ንግድ ላይ ተሰማርቷል።