(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 19/2011)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ እና በውጭ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊ የነበሩት ብጹዕ አቡነ መልከጸዲቅ እሑድ አዲስ አበባ ይገባሉ።
ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በስደት የቆዩት ብጹዕ አቡነ መልከጸዲቅ ከጤና ጋር በተያያዘ ከፓትርያሪክ አቡነ መርቆርዮስ ጋር ለመመለስ አለመቻላቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
በሐምሌ ወር 2010 በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ዕርቅ ሲያደርጉ ከካሊፎርኒያ ወደ ዋሽንግተን የመጡትና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ጋር የተገናኙት ብጹዕ አቡነ መልከጸዲቅ በውጭ በነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው አባት እንደነበሩም መረዳት ተችሏል።
በቀድሞው የደርግ መንግስት ወደ ወህኒ ከተጋዙ የሃይማኖት አባቶች አንዱ የነበሩትና በንጉሱ ዘመን በኢትዮጵያ ሬዲዮ መንፈሳዊ ትምህርት በመስጠት የሚታወሱት አቡነ መልከጸዲቅ ለ8 ዓመታት ያህል ወህኒም ቆይተዋል።
ኢህአዴግ ወደ ስልጣን እንደመጣ አቡነ መርቆሪዎስ ከፓትርያርክነታቸው በመንግስት ትዕዛዝ ሲወገዱ ድርጊቱን በማውገዝ ከፓትርያርኩ ጋር ከተሰደዱት አባቶች አንዱ የነበሩት ብጹዕ አቡነ መለከጸዲቅ በስደት ላይ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ በመንፍሳዊና በሀገራዊ ጉዳይ በማስተማርና በማስተባበር በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 27 ዓመታት በህዝብ ላይ የሚደርሱ በደሎችን ሲቃወሙና መንግስት ከግፍ ድርጊቱ እንዲታቀብ ሲያሳስቡም ቆይተዋል።
ከ5 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች በድምጻችን ይሰማ ኮሚቴ አባላትና መሪዎች ላይ የተወሰደውን ርምጃ በአደባባይ በማውገዝም ብጹዕ አቡነ መልከጸዲቅ አጋርነታቸው አሳይተዋል።
ሃገር የጋራ ሃይማኖት የግል ነው በወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቁም በሚል በአደባባይ ያቀረቡት ጥሪ በአልጀዚራ ቴሌቭዥን ጣቢያ መተላለፉም ይታወሳል።
ብጹዕ አቡነ መለከጸዲቅ ከተለያዩ ዓለማት የክበር ሽልማት ያገኙ ሲሆን ከግሪክ መንግስትና ቤተክርስቲያን ፣ከኦስትሪያና ከእስክንድሪያ ቤተክርስቲያን የሚጠቀሱ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ አቡነ መልከጸዲቅ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በካሊፎርኒያ ግዛት ካሉ አምስት ከንቲባዎች የምስክር ወረቀት እንዲሁም የከፍተኛ የህይወት ዘመን ተሸላሚ እንዲሆኑ ተወስኖላቸዋል።
የትውልድ ቀናቸው ሐምሌ 19ም በየአመቱ የአቡነ መልከጸዲቅ ቀን እንዲሆን መወሰኑም ይታወሳል።
የ94 ዓመቱ አዛውንትና የሃይማኖት አባት ብጹዕ አቡነ መልከጸዲቅ ከ27 ዓመታት በኋላ ዛሬ ከመኖሪያቸው ኦክላንድ ካሊፎርኒያ ተነስተው በነገው ዕለት ከዋሽንገትን ዲሲ ወደ ኢተዮጵያ በመጓዝ ሕሁድ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎም ይጠበቃል።