የካቲት ፲ ( አሥር )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመከላከያ ሚኒስቴር ስር የሚገኘውና አብዛኛውን የመከላከያን ግዢ በኮንትራት ወስዶ የሚሰራው የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ) ሰው አልባ የስለላ አውሮፕላኖችን በአገር ውስጥ ለማሰራት ከ235 ሚሊዮን 500 ሺ የአሜሪካን ዶላር ወይም 4 ቢሊዮን 710 ሚሊዮን ብር መክፈሉን ከድርጅቱ የተገኙ የሂሳብ መዝገብ ሰነዶች አመለከቱ።
ብኢኮ በፈንጆች አቆጣጠር ከ2011 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ብቻ ከ1 ቢሊዮን 372 ሚሊየን 881 ሺ 730 ዶላር ወይም ከ27 ቢሊዮን 457 ሚሊዮን 634 ሺ 600 ብር ወታደራዊ ግዢ የፈጸመ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ግዢዎች ከፍተኛ ወለድ በሚያስከፍል እዳ የሚፈጸሙ ናቸው።
ብኢኮ ለቱርኩ MIL –YAZ ኩባንያ ሰው አልባ አውሮፕላን ለማሰራት joint design and development of UAS system ለማሰራት 33 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል የተዋዋለ ሲሆን፣ ከእስራኤሉ ብሉ በርድ ኩባንያ (BLUEBIRD AERO SYSTEMS) ጋር ደግሞ UGV and MAB የተባሉ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን መሳሪያዎች በጋራ ለማሰራት 22 ሚሊዮን 55 ሺ ዶላር ከፍሏል። እንዲሁም Joint design and Development of TBO ለተባለ ፕሮግራም ደግሞ 180 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መክፈሉን ሰነዶች ያመልክታሉ።
አብዛኛው ወታደራዊ ግዢዎች የሚፈጸሙት ከቻይናው ፖሊ ኩባንያ ጋር ሲሆን፣ ብኢኮ በአንድ አመት ውስጥ ብቻ 724 ሚሊዮን 567 ሺ 647 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በመከላከያ ስም ገዝቷል። ከዚህ ኩባንያ ጋር ለ strategic partnership የሚል ድፍን ያለና በዝርዝር ያልተገለጸ የ500 ሚሊዮን ዶላር የክፍያ ስምምነት የተቀመጠ ሲሆን፣ ብኢኮ ለኩባንያው 30 በመቶ ቅድመ ክፍያ እንደፈጸመ ያሳያል። ይህ ለጋራ ስትራቴጂ ወዳጅነት ተብሎ የተፈረው ስምምነት በውስጡ ዝርዝር መረጃዎችን ያልያዘ በመሆኑ ምናልባትም የተፈጸመ ሙስናን ለመሸፋፈን የተደረገ ሳይሆን እንደማይቀር ሰነዱን ያወጡት የኢሳት ምንጮች ግምታቸውን ይገልጻሉ።
ሌላው የግዢ ስምምነት የተፈጸመው ከቻይናው Aerospace Long-March International Trade Co ጋር ሲሆን፣ Portable surveillance radar microwave and digital testing equipment እና Ly -60D surface to air missile system ለመግዛት 150 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል።
NORNICO ከተባለ የቻይና ኩባንያም ጋር እንዲሁ 440 ሚሊዮን 157 ሺ 409 ዶላር የሚያወጣ ወታደራዊ ግዢ የተፈጸመ ሲሆን፣ ከዚህ ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነት በአብዛኛው ከሮኬት ግዢ ጋር የተያያዘ ነው። ሰነዱ ቻይና በሲቪል ግንባታ ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ ቁሳቁሶች ሽያጭ ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላትና ቀዳሚዋ ወታደራዊ ቁሳቁስ አቅራቢ አገር መሆኗን የሚያመለክት ነው። ከቻይና በመቀጠል ዩክሬንና ቱርክ ከገዢው ፓርቲ ጋር የጠበቀ ወታደራዊ ግንኙነት እንዳላቸው ሰነዱ ያመለክታል። በታንክ ሽያጭ ዩክሬን ቀዳሚ አገር ስትሆን፣ ሩስያ በሁለተኛ ደረጃ ትገኛለች።
ብኢኮ በራሳችን አቅም ሰው አልባ አውሮፕላን ለመስራት እየሞከርን ነው በሚል በመገናኛ ብዙሃን ሲያስነግር የቆየ ቢሆንም፣ ሰነዱ እንደሚያሳየው ግን ስራውን የሚያከናውነው የቱርኩ የወታደራዊ ቴክኖሎጂ አምራች ኩባንያ MIL –YAZ ነው። ብኢኮ አብዛኛውን ወታደራዊ ግዢዎች የሚፈጽመው የተሻለ የግዢ ስርዓት ከሚከተሉ የምእራባውያን አገራት ሳይሆን፣ በሙስና እና ጥቅማጥቅሞችን በመስጠት ከሚወቀሱ የምስራቅ አገራት ጋር መሆኑ፣ የኩባንያው ወታደራዊ አዛዦች ይፈጽሙታል እየተባለ በተደጋጋሚ የሚዘገበውን የሙስና ዜና የሚያጠናክር ይሆናል። አብዛኞቹ ግዢዎች በቂ ጥናት እና ምርመራ ሳይደረግባቸው የሚፈጸሙ በመሆኑ፣ ብዙዎቹ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው ከተገዙ በሁዋላ ጥቅም ላይ ሳይውሉ ይበላሻሉ። ግዢዎችን ከድለላ ጀምሮ እስከ ግዢ የሚፈጽሙት የህወሃት የመከላከያ አዛዦች ብቻ ናቸው።
በኢትዮጵያ ከሚታየው ተደጋጋሚ ድርቅ እና የኑሮ ውድነት አንጻር ይህን ያክል ገንዘብ በማውጣት ወታደራዊ የግዢ ስምምነቶችን መፈረም ተገቢ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በአሁኑ ሰአት ከ5 ሚሊዮን 600 ሺ በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህን ለመደጎም ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል። አብዛኛው በድርቅ የተጠቁት አርብቶአደሮች የቤት እንስሶቻቸውን ወደገበያ እያወጡ በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡና ራሳቸውን እንዲመግቡ እየተገደዱ ነው።