(ኢሳት ዜና–ጳጉሜ 3/2009)የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ የአማራ ግጨው ሁለት መንደሮችን ለትግራይ አስረክቦ በራሱ ግዛት ያለን የእርሻ መሬት ቦታ አገኘሁ ማለቱ ታሪካዊ ስህተት መሆኑን በአካባቢው የመሬት አስተዳደር ባለስልጣን የነበሩ ሰው ገለጹ።
በአማራና በትግራይ ክልሎች ርእሰ መስተዳድሮች ስምምነት ለትግራይ የተሰጡት የግጨውና የጎቤ መንደሮች ከዚህ ቀደም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ የአካባቢው ሕዝብ አማራ ነን በማለቱ ውሳኔ አግኝቶ ነበር።
ነገር ግን ውጤቱ ታፍኖ ከቆየ በኋላ ትግርኛ ተናጋሪዎችን አስርጎ በማስገባት አካባቢውን በጉልበት መውሰዳቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቀድሞው መሬት አስተዳዳሪ ባለስልጣን ለኢሳት ገልጸዋል።
የአማራ ክልል አገኘሁ በማለት የደስታ መግለጫ ያወጣባቸው የሟይምቧይና ሰላንዴ ረግረግ የእርሻ ቦታዎች ቀድሞውንም የራሱ የነበሩ ቦታዎች በመሆናቸው ሁኔታው ያስገርማል ብለዋል።
የመሬት አስተዳደር ባለሙያው እንዳሉት የትግራይ ገዥዎች ይሉኝታ የማያውቁና ሀፍረተ ቢሶች ናቸው።
እንደሳቸው አባባል ሕወሃት ስልጣን ከያዘ በኋላ ወልቃይትን ከአማራ ክልል መንጠቃቸው ሳያንስ ከሶርቃ ወንዝ ተሻግሮ በመምጣት ግጨውን ይገባኛል ማለታቸው አስገራሚና ይሉኝታ ቢስነት ነው።
ባለሙያው እንደገለጹት ሕወሃት በጉልበት መሬት መንጠቅ ከመጀመሩ በፊት የጠገዴ አካባቢ በሙሉ የአማራ ተወላጆች ነበር።በኋላ ግን ጠገዴና ጸገዴ በሚል ከሁለት ከፍለው መሬቱን በሃይል መንጠቃቸውን የቀድሞው የመሬት አስተዳደር ባለሙያ ገልጸዋል።
እንደ ቀድሞው የመሬት አስተዳደር ባለሙያ ገለጻ የአማራ ክልል የወሰን መስመር የተዘረጋው የተከዜን ወንዝ ተከትሎ ነበር።
አሁን ግን የሕወሃት ገዥዎች በማን አለብኝነት በርካታ የአማራ መሬቶችን በጉልበት ዘርፈዋል ነው ያሉት።
እንደ መሬት አስተዳደር ባለሙያው የአማራና የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድሮች ሰሞኑን ተስማሙ ተብሎ የተገለጸው ጉዳይ እጅግ አስገራሚና አስቂኝ ነው።
በስምምነቱ የግጨውና የጎቤ ሁለት መንደሮች ለትግራይ ክልል የተሰጡት ሕገወጥ በሆነ መንገድ በብአዴን ይሁንታና በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለዘብተኝነት ነው።
ከዚህ ቀደም የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ አያሌው ጎበዜ የትግራይ ተስፋፊዎች ሶርቃ ወንዝን በመሻገር በግጨው አካባቢ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ማንሳታቸውን በጽኑ ተቃውመው ነበር።
አሁን ግን የአሁኖቹ የክልሉ ባለስልጣናት በትግርኛ ተናጋሪዎች ሆን ተብለው እንዲወረሩ የተደረጉት የግጨውና ጎቤ ሁለት መንደሮችን ለትግራይ ክልል አስረክበዋል ብለዋል።
ብአዴን የአማራ ክልል ቦታ የሆኑትን የሟይምቧይና ሰላንዴ የእርሻ ቦታዎችን አገኘን ብለው ማለታቸው በሕዝቡ ላይ እንደማፌዝ ይቆጠራል ነው ያሉት።
ስለሆነም በብአዴን የሚመራው የአማራ ክልላዊ መንግስት የራሱን መንደሮች አስረክቦ በራሱ መሬት ያለን የእርሻ ቦታ አገኘሁ ማለቱ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
እናም እያንዳንዱ የአማራ ተወላጅ ጉዳዩን አጥብቆ በመከታተል ሕልውናውን እንዲታደግ የቀድሞው የመሬት አስተዳደር ባለሙያው ጥሪ አቅርበዋል።