ኀዳር ፲ (አስር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ህዳር 9፣ 2008 ዓም ብአዴን በሰልፉ ለመሳተፍ የሚፈልገውን አሽከርካሪ ማግኘት ባለመቻሉ የባጃጅ ማህበር አመራሮችን በመንገድ ትራንስፖርት አማካኝነት በመጥራት በሰልፉ ባይሳተፉ የአምስት መቶ ብር ቅጣት እንደሚፈጽም በማስፈራራት ከቀኑ 10፡30 እስከ 11፡30 መንገዶችን በመዘጋጋት ህብረተሰቡን ሲያስጨንቅና ባጃጆችን ተሰለፉ በማለት ሲያሳድድ እንደነበር ዘጋቢያችን ገልጻለች።
የባህርዳር ነዋሪዎች ብአዴን በዓሉን ብቻውን እያከበረ መሆኑን ያየንበት ክስተት ነው ብለዋል። ሰሞኑን በዓሉን አስመልክቶ በተፈጠረው ውጥረት ህብረተሰቡ ስራውን በአግባቡ ለመስራት አልቻለም፡፡የምሽት አገልግሎት የሚሰጡ ባጃጆች እንዳይሰሩ በመታገዳቸው ከምሽቱ 3፡00 በኋላ የታክሲ አገልግሎት ህብረተሰቡ ባለማግኘቱ በእግር ለመጓዝ ተገዷል፡፡ በሰማዕታት ሃውልት ውስጥ ደግሞ እያንዳንዱ ሴክተር መስሪያ ቤት በግድ እንዲያዘጋጅ በተደረገው የፎቶ ግራፍ ኢግዚቢሽን አንድም የከተማው ነዋሪ አለመመልከቱ እንዳሳፈራቸው የበአሉ ታዳሚ ሰራተኞች እየተናገሩ ነው፡፡ የኢግዚቤሽኑን ውሎ አሳፋሪ ሲሉ አስጎብኝዎች ገልጸውታል፡፡
ህዳር 5 ቀን 2008 ዓም ደግሞ ከአዘዞ የመምህራን መኖሪ ወደ ማራኪ ግቢ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሰርቪስ መኪና መምህራን ሲጓዙ፣ ሹፌሩ ሳይንስ አመባ ወደ ተዘጋጀው የብአዴን በአል ሲያመራ፣ በመኪናዉ የነበሩት መምህራን የት ነዉ የምትወስደን ብለው ሹፌሩን ሲጠይቁት “ወደ ሳይንስ አምባ መሰብሰቢያ አዳራሽ አምጣቸዉ ተብያለሁ” ብሎ በበመለሱ፣ መምህራን “በማናምንበትና በማይመለከተን ስብሰባ አንሄድም” በማለታቸው ሹፌሩ መኪናዉን ለመመለስ ተገደዋል። መምህራኑን በዝግጅቱ ሳይገኙ ቀርተዋል ። ከፍተኛ ድርቅ በተከሰተበት በዚህ ወቅት ብአዴን 300 ሚሊዮን ብር በማውጣት በአሉን እያከበረ ነው።
በሌላ ዜና ደግሞ አቶ ደመቀ መኮንን በሰሜን ጎንደር ዞን የተዘጋ ትምህርት ቤት ስለመኖሩ አላውቅም አሉ። አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ደመቀ መኮንን ከቅማንት ብሄረሰብ ተወካዮች ጋር ከትናንት በስቲያ ጎንደር ከተማ ውስጥ ስብሰባ ያደረጉ ቢሆንም ያለ ውጤት ተበትኗል። ተወካዮች 159 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ሲናገሩ፣ ም/ል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልሰማሁም ማለታቸው ተወካዮችን በእጅጉ አበሳጭቷል።
ንጹሃን ዜጎችን በግፍ የገደሉት ይጠየቁልን የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡም፣ ከእናንተ ጀርባ ሆነው የሚወጉን አሸባሪዎች እንጅ ንጹሃን ዜጎች አልተገደሉም፣ እንዲያውም በብዛት የተገደሉት የጸጥታ ሃይሎች ናቸው የሚል መልስ ሰጥተዋል።
ላነሳችሁት ጥያቄ መልስ እንሰጣለን ከማለት ውጭ ምንም የተለዬ ነገር አለመናገራቸውን ስብሰባውን የተካፈሉ ወገኖች ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለት አረንጓዴ ዩኒፎርም የለበሱ የጸጥታ ሃይሎች ከትናንት በስቲያ ተገድለው አስከሬናቸው በአካባቢው ነዋሪዎች ተነስቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች የታሰሩ ሲሆን፣ እጃችን አንሰጥም በማለት የሸፈቱ የመንግስት ሹሞች መኖራቸውም ታውቋል።