(ኢሳት ዜና–መስከረም 23/2010)በሕዝብ ተወክሏል ለሚባለው የአማራ ክልል ምክር ቤት ቀርቦ ሳይጸድቅ ብአዴን የቢሮ ሐላፊዎችን ማቀያየርና መመደብ መጀመሩን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ብአዴን ሰሞኑን ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ የክልሉን ካቢኔ አባላት በክልሉ ምክር ቤት እንዲጸድቅ ሳይደረግ ስራ ያስጀመራቸውም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።
በአዲሱ ምደባ የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ሃላፊ አቶ ፍስሃ ወልደሰንበት ከሃላፊነት ተነስተው በምትካቸው አቶ እዘዝ ዋሴ መመደባቸው ይነገራል።
አቶ ፍስሃ ወልደሰንበት ወደ ግብርና ቢሮ ሲወሰዱ የሌሎችም ካቢኔ አባላት በብአዴን ተወስኖ ሹም ሽሩ ውስጥ ውስጡን ተግባራዊ ተደርጓል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብአዴን ካድሬዎች ግምገማ ላይ የታየው ተቃውሞና ድፍረት ለሕወሃት አስጨናቂ በመሆኑ ምደባው ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን የቅርብ ምንጮች እየገለጹ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በአማራ ክልል የተመደቡ ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ ለስራ ሲሄዱ መኪናቸውን መያዝ እንደሌለባቸው መመሪያ ወጥቷል።
እንደምንጮቻችን ገለጻ የአማራ ክልል ባለስልጣናት አዲስ አበባ ለስራ ሲሄዱ ካሁን በኋላ አገልግሎት የሚሰጣቸው በኢፈርት ስር ያለው የትራንስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ነው።
የአማራ ክልል ባለስልጣናት መኪና እንዳይዙ የተወሰነባቸው ወጭን ለመቆጠብ ነው ቢባልም በትራንስ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጠቀሙ የሚደረጉት ለክትትል እንዲያመች ነው መባሉን የሚናገሩ መኖራቸውን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።