መጋቢት ፳፪ (ሃይ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የህወሀት ጉዳይ አስፈጻሚ እየተባለ ተደጋጋሚ ትችት የሚደርስበት የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ወይም ብአዴን፣ ከደቡብ ክልል በቤንች ማጅ ዞን በጉራ ፋርዳ ወረዳ በግፍ ተፈናቅለው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ወደ 200 የሚጠጉ የአማራ ተወላጆችን ተጠልለው ይገኙበት ከነበረው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲወጡ በማድረግ በሁለት ማጎሪያ ካምፖች እንዲቀመጡ አድርጓል።
ተፈናቃዮቹ ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ በስላሴ ቤተክርስቲያን ለመጠለል ጥያቄ ሲያቀርቡ በችግር ጊዜ መጠለያ ትሆናለች ተብላ የምተታመነዋ ቤተክርስቲያን አላውቃችሁም ብላ በማሰናበቱዋ ህዝበ ክርስቲያኑን ማሰዘኑ ይታወሳል። በጉዳ የተበሳጨው መኢአድ ሁሉንም ስደተኞች የሀይገር አውቶቡስ በመከራየት ወስዶ በግቢው ውስጥ ሰፊ ድንኳን በመትከል ሲንከባከባቸው ቆይቷል። ጉዳ የመገናኛ ብዙሀን ትኩረትን ከሳበ በሁዋላ በአዲስ አበባ እና በመላው አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ቁጣ በመቀስቀሱ የከተማው ቀዳሚ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል። በአገር ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶች በውጭ አገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር በመነጋጋር ተፈናቃዮችን ለመርዳት ሰፊ የእርዳታ ማሰባሰብ ዝግጅት እያደረጉ በነበረበት ጊዜ ፣ ሲፈናቀሉ አላውቃችሁም ያላቸው ብአዴን በትናንተናው እለት ተፈናቃዮች ከመኢአድ ግቢ እንዲወጡ አድርጓል።
የእርዳታ መርሀ ግብሩን በመዘርጋት ሲሳተፍ የነበረ አንድ ስሙ እንዳይገለጥ የፈለገ ሰው ለኢሳት እንደገለጠው የብአዴን ተወካዮች ወደ መኢአድ ጽህፈት ቤት በመሄድ ፤ ከብአዴን ተወክለን የመጣን ነን በማለት ሰዎቹ ከግቢው እንዲወጡ አስደርገዋል። ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ጊዜ ከስላሴ ቤተክርስቲያን ጀርባ እና የካቲት 12 አካባቢ በሚገኝ ሁለት የማጎሪያ መጋዘኖች ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ለማወቅ ተችሎአል። ሰዎቹ ከቤት እንዳይወጡ፣ ከማንም ሰው ጋር እንዳይገናኙ በመደረጉ ስላሉበት ሁኔታ ለማወቅ ፈጽሞ አልተቻለም። በአካባቢው የሚወጡ ያልተረጋገጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ቃለምልልስ የሰጡ ተፈናቃዮች እየተደበደቡ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት በድርጊቱ በአዴን በከፍተና ደረጃ አፍሮአል፣ መኢአድም ከፍተኛ የፖለቲካ ትርፍ አግኝቷል፣ በዚህ የተበሳጨው ብአዴን ሰዎቹን ያለምንም ዝግጅት ከመኢአድ ግቢ እንዲወጡ በማድረግ ከማንም ሰው ጋር እንዳይገናኙ ግቢውን በወታደር እያስጠበቀ ነው።
የብአዴን ድርጊት ያስቆጣቸው አንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ ግለሰቦቹ ከተፈናቀሉት በላይ ብአዴን እስር ቤት ውስጥ መክተቱ ለሰዎቹም ለወገኖቻቸውም ሞት ነው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሁለት አይሲዙ የተሳፈሩ ሌሎች የአማራ ተፈናቃዮች ዛሬ ጧት አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን ድረስ አለመግባታቸው ታውቋል። የተፈናቃየቹን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ ሰው እንዳሉት ተፈናቃዮቹ ከአካባቢው ተሳፍረው መንገድ መጀመራቸውን ያረጋገጡ ቢሆንም ከተወሰነ ሰአት በሁዋላ የት እንደደረሱ ለማወቅ ሙከራ ቢያድርጉም ሳይችሉ ቀርተዋል። ተፈናቃዮቹ አዲስ አበባ መድረስ በሚገባቸው ሰአት ባለመድረሳቸውም መንግስት ወደ ሌላ አቅጣጫ ወስዷቸዋል የሚለውን ግምት አጠናክሮታል። በደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ መመሪያ የተፈናቀሉ ከ20 እስከ 70 ሺ የሚጠጉ የአማራ ተወላጆች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ከትናንት በስቲያ ባወጣው አስቸኳይ ጥሪ የአለም መንግስታት እና ድርጅቶች ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲያድረጉ ጥሪ አቅርቧል።
ሰመጉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ተፈናቃዮች ለአመታት ያፈሩትን ቤት ንብረት በትነው በተለያዩ ከተሞች እንዲባዝኑ መደረጉ አለማቀፍ ህግን የሚጥስ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ፣ የተወሰደባቸው ንብረት እንዲመለስ እና ተገቢው የመኖሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቋል።
በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ድርጊቱ የዘር ፖለቲካው አስከፊ ውጤት ነው ይላሉ። ሌሎች ወገኖች ደግሞ የአሁኑ እርምጃ የመለስ መንግስት ለአለፉት 20 አመታት በአማራ ህዝብ ላይ ሲፈጽም የነበረው ጥቃት ተቀጥያ ነው ይላሉ። የቤንች ማጂ ዞን ተወላጆች ለተፈናቃዮቹ ያሳዩት የነበረው ርህራሄ ህዝቦችን በማጋጨት የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ለሚሞክረው የመለስ መንግስት ስልቱ የሚሳካ አለመሆኑን ለማሳየት ጥሩ ትምህርት የሰጠ ነው በማለት ኢሳት ያነጋገራቸው በአገር ቤት የሚገኙና ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ የፖለቲካ መሪዎች ተናግረዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide