ብአዴን አቶ ደመቀ መኮንን የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው እንዲቀጥሉ ወሰነ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 16/2010)

የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/አንድ ወር ለሚሆን ጊዜ ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ምንም ለውጥ ሳያደርግ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ሆነው እንዲቀጥሉ ወሰነ።

በምክትል ሊቀመንበርነት ደግሞ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባሉበት እንዲቀጥሉ በማዕከላዊ ኮሚቴው ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ብአዴን ለየት ያለ ውሳኔ አሳልፋለሁ ቢልም ሁኔታዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ መወሰኑ በብዙዎች ዘንድ ግርምታን ፈጥሯል።

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ታይቶ የማይታወቅ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለምነው መኮንን በቅርቡ ገልጸው ነበር።ለአንድ ወር ያህል በባህር ዳር ከተማ የተካሄደውን የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መጠናቀቅ ተከትሎ የወጣው መግለጫ ግን አልሸሹም ዞር አሉ የሚለውን አባባል አስታውሷል።የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ ደመቀ መኮንን የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ባሉበት እንዲቀጥሉ ወስኗል።የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ የአቋም መግለጫም ከወትሮው የተለየ እንዳለሆነ በዝርዝሩ ውስጥ የተገለጹ ጉዳዮች ያመለክታሉ።ብአዴን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረጉን፣የከተሞችም ትንሳኤ መታየቱን በማድነቅና ለራሱ ትልቅ ዋጋ በመስጠት ሽልማት ከራሱ ተቀብሏል።ብአዴን ይህን ይበል እንጂ በክልሉ ኢንደስትሪ አለመኖሩን እና በዚህ አቅጣጫ ገና ከእንግዲህ እንደሚሰራ ገልጿል።በክልሉ ያለውን የሕዝብ ተቃውሞም የሕገ ወጦችና ሰላምን የማይፈልጉ ሃይሎች ስራ ነው ሲል በማናናቅ ይህንኑ ለማስቆም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቋል።ሙስና እና ብልሹ አሰራር በክልሉ ተንሰራፍቷል ያለው የብአዴን መግለጫ የእርምት ርምጃ ይወስዳል ከማለት ውጪ በአንድም ባለስልጣን ላይ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከሃላፊነት ስለመነሳቱ የገለጸው ነገር የለም።በፌደራል ስርአቱ ውስጥ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉድለት እንዳለ ቢያምንም ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት ይደረጋል ከማለት ውጭ ማብራሪያ አልሰጠም።ብአዴን ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አብረን እንስራ ሲልም የድጋፍ ጥሪ አስተላልፏል።ብአዴን አቶ ደመቀ መኮንን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ ባሉበት እንዲቆዩ ያደረገው በተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩ አድርጎ ለማቅረብ ስለመሆኑ የገለጸው ነገር የለም።አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ግን የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲቀጥሉ የወሰነው ከሕወሃት ፍላጎት ውጪ ነው ተብሏል።