ብአዴን አቶ ደመቀንና አቶ ገዱን በስልጣን ላይ ለማቆየት ወሰነ
(ኢሳት ዜና የካቲት 16 ቀን 2010 ዓ/ም) በዝግ ስብሰባ ለሳምንታት ሲገማገም የሰነበተው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ አቶ ደመቀ መኮንን የድርጅቱ ሊ/መንበር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ደግሞ የድርጅቱ ምክትል ሊ/መንበር ሆነው እንዲቀጥሉ ውሳኔ አሳልፏል።
አቶ ገዱ በሌሎች ሰዎች እንደሚተኩ አስቀድሞ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ግን ድርጅቱ በእርሳቸው መሪነት መቀጠሉን መርጧል። አቶ አለምነው መኮንን ብአዴን ከአመራር ለውጥ ጀምሮ ከዚህ ቀደም ያልተለመዱ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብለው የተናገሩ ቢሆንም፣ ድርጅቱ በነባር አመራሮቹ መቀጠልን መርጧል።
ለህወሃት ታማኝ ናቸው የሚባሉት አቶ አለምነው መኮንንና አቶ ከበደ ጫኔ ከፍተኛ የውስጥ ትግል ሲያደርጉ ሰንብተዋል።
ብአዴን ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ፣ “በፌደራል ስርዓታችን ውስጥ የፍትሃዊነት መጓደል የሚታይባቸውን ማናቸውም ዘርፎች የማስተካከል ስራ እንዲሠራና ለወደፊቱም ጥርጣሬ የሚያነግሱ መሰል ተግባራት እንዲታረሙ ተገቢ ትግል እንዲደረግ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡” ብሎአል።
ብአዴን “ የአመለካከት ልዩነታችን ሳይገድበን ዘለቄታ ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ” ነኝ ብሎአል።
ብአዴን በአማራ ክልል ውስጥ የተለያዩ አስተሳሰቦች በነፃነት የሚራመዱበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እና ይህንኑ በመተግበር ረገድ ጉድለት እንዳለ ፣ ከመልካም አስተዳደር አኳያ ህብረተሰቡን ያማረሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች፣ የሠብአዊ መብት አያያዝ ጉድለት፣የኑሮ ውድነት ፣ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ችግር ፣ ህገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ ፣ህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ የወጣቶች የስራ ዕድል ችግር እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ በመግለጫው ጠቅሷል።