ብአዴን ባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካን መጠቅለሉንና ዳሸን ቢራ በኪሳራ እየማቀቀ መሆኑን አስታወቀ

የካቲት ፳፫ ( ሃያ ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የብአዴን የልማት ድርጅት የሆነው ጥረት ከርፖሬት ሰሞኑን በዋና ስራ አስፈፀሚው አቶ ታደሰ ካሳ በሰጠው መግለጫ ፣ ኮርፖሬቱ በአሁኑ ስዓት በርካታ ፋብሪካዎችን በመያዝ በክልሉ ቀዳሚ መሆኑን እንዲሁም ከኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ለደረሰው ግፍ የደም ካሳ ክፍያ ተብሎ የተገነባውን የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን መጠቅለላቸውን ተናግረዋል። በዳሸን ቢራ ግን ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶብናል ብለዋል።
ጥረት በዳሸን ከደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ ውጭ በተለያዩ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ኪራይ እና አገልገሎት ከመንግስት ጋር በቀጥታ ያለ ጫረታ ባገኛቸው ድጋፎች 1 ቢልየን 442 ሚልየን 876 ሽህ ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል።
ዳሽን ቢራን መጠጣት ደም እንደመጠጣት አድርጎ የሚያየውን ድርጅት ከመዘጋት ለማትረፍ በሚሊዮን የሚቀጠር ገንዘብ እየከፈለ የተለያዩ አርቲስቶችን በመጋበዝ ለማስተወዋቅ ቢሞክርም፣ ጥረቱ አድካሚ እና አሰልች እየሆነ መምጣቱን አቶ ታደሰ ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ጥረት ላገኘው ትርፍ አስተዋጽኦ ያደረጉት አምባሰል የንግድ ስራዎች ድርጅት ፣ ጥቁር ዓባይ ትራንስፖርት ድርጅት እና ኮልቻ ትራንስፖርት አክሲዩን ማህበር ናቸው። በ2016 ኮርፖሬቱ ያለመውን ገቢ ያላገኝበት ፣ ያልተሳኩ ሽያጮች የተበራከቱበት፣ ህዝባዊ አመፁ ብትሩን ያሳረፈበት እንዲሁም የውጭ ምዛሬ እጥረት እና የግበዓት እጥረት በማጋጠሙ ነው ሲሉ ስራ ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
አቶ ታደሰ ካሳ ከኢጣልያ መንግስት ለኢትዮጵያውን በደም ካሳነት የተበረከተውን የባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እና የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን በሰባት መቶ ሚልየን ብር መግዛታቸውን ቢገልጹም፣ ሰራተኞችና ነዋሪዎች ግን ባዶ ቦታዎች ብቻ ሰባት መቶ ሚሊዮን ብር እንደሚያወጡና ብአዴን ጉልበቱን በመጠቀም የደም ካሳ የሆነውን የህዝብ ሃብት እንደዘረፈ ይናገራሉ።
በገበያ እጦት የተመታው ሌላው የድርጅቱ ኩባንያ የጣና ኮምንኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን ይህንን ለማካካስ በቀጣይ አመታት አርሶ አደሩ ከአንድ ሽህ ብር ጀምሮ አክሲዎን እንዲገዛ በማድረግ፣ የወረቀት ፣ የልብስ ስፊት እና የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት ስራ እየተጠናቀቀ ነው፡፡