(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 5/2011) ብርጋዴር ጄኔራል ሃይሉ ጎንፋ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሾሙ።
በሳምንቱ መጨረሻ ብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹና ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች የጸጥታ ከፍተኛ ሃላፊዎች ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።
በምርጫ 1997 በኢትዮጵያውያን ላይ የተካሄደውን ጭፍጨፋ በመቃወምና፣የምርጫውን መጭበርበር በማውገዝ ሰራዊት ይዘው ወደ ኤርትራ የገቡት ብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹ የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ ሆነው በሳምንቱ መጨረሻ መሾማቸው ተሰምቷል።
ከእሳቸው ጋር በተመሳሳይ ሰራዊቱን አስከትለው ኤርትራ የገቡት ሌተናል ኮሎኔል አበበ ገረሱ የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሆነው መሾማቸው ተመልክቷል።
በነሐሴ ወር 1998 ሰራዊት አስከትለው ኤርትራ የገቡትን ሁለት ከፍተኛ መኮንኖች በመከተል በተመሳሳይ የመንግስትን የአፈናና የግድያ ድርጊት በማውገዝ በመስከረም 1999 ኤርትራ የገቡት ብርጋዴር ጄኔራል ሃይሉ ጎንፋ የኦሮሚያ ክልል የፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።
እነዚህ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ስርአቱን ከድተው ኤርትራ ከገቡ በኋላ ኦነግን በመቀላቀል በትግሉ ውስጥ ቆይተዋል።
ከኦነግ ጋር ባለመስማማት ከድርጅቱ ቢለዩም በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ታቅፈው ሲታገሉ ቆይተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትለው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት እነዚህ ሶስት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መሾም የኦሮሚያ ክልል ጸጥታን በማሻሻል ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስተያየት ሰጭዎች ይገልጻሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በምርጫ 1997 በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝና የምርጫውን መጭበርበር በመቃወም እንቅስቃሴ አድርጋችኋል በሚል ማዕረጋቸው ከተገፈፈባቸው ጄኔራሎች አንዱ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የአማራ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል።
የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ዋና ሃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ በነበረበት ወቅት ከቀድሞው አየር ሃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አለምሸት ደግፌ ጋር ማዕረጋቸውን የተገፈፉት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በ2001 አመተ ምህረት በመፈንቅለ መንግስት ተጠርጥረው ከነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ ጋር መታሰራቸው ይታወሳል።
ለ10 አመታት ያህል በወህኒ ቆይተው ከእስር የወጡት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በአማራ ክልል ከፍተኛውን የጸጥታ ሃላፊነት መያዛቸው ለክልሉ ጸጥታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተመልክቷል።
ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር በመፈንቅለ መንግስት ተጠርጥረው ታስረው በወህኒ የቆዩት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞና ሌሎቹም ከፍተኛ መኮንኖች በፌደራልና በክልል ልዩ ልዩ ስልጣን ሊሰጣቸው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።