(ኢሳት ዜና ሐምሌ 7/2009) በአዲስ አበባ በቡልጋሪያ ማዞሪያ አካባቢ የሚገኘው ብርሃን የኢትዮጵያ የባህል መአከል በህገወጥ መንገድ እየፈረሰ መሆኑ ተነግሯል።
ማዕከሉ እንዲፈርስ የተፈለገው ከቦሌ ወደ አፍሪካ ህብረት የሚወስደው መንገድ መተላለፊያ በመሆኑ ነው ተብሏል ።
መንገዱ ከተጀመረ ሁለት አመት ቢሆነውም የኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ጉዳዩ ሳይነገራቸው ከአጥር ግቢው 5 ሜትር ያህል ፈርሶ እንዳገኙትና በህገወጥ መንገድ አፍራሽ ግብረሀይል እንደተላከባቸው ገልጸዋል።
ማዕከሉ በ960 ስኩየር ሜትር ላይ ያረፈና የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ቅርሶች በመያዝ ለጎብኚዎች በአንድ ግዜ ለማስቃኘት የሚያስችል ነው።
በማዕከሉ የአክሱም ሃውልት የፋሲል ግንብ እንዲሁም ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርሶች ይገኙበታል ።
የኢትዮጵያ የባህል ማእከል ሙሉ በሙሉ እንዳይፈርስባቸው የቂርቆስ ክፍለ ከተማን ጨምሮ ለአዲስ አበባ አስተዳደር እንዲሁም ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቢያመለክቱም ምላሽና ሰሚ እንዳላገኙ ወ/ሮ ሳቤላ ገልፀዋል።
ብርሃን ኢትዯጵያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1987 በፔሩ ሊማ የተመሰረተ ሲሆን ወደ ሀገር ቤት የመጣውም የወ/ሮ ሳቤላ ጓደኛ ወ/ሮ አማረች ታደመ ቤታቸውን ለዚሁ ዓላማ እንዲውል በነፃ በመለገሳቸው መሆኑ ይነገራል።
የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል በከፍተኛ ወጪ የተሰበሰቡ ልዩ ልዩ ቅርሶችን በመያዙ ያለምንም ማስጠንቀቂያ መውድሙ እንደሚያሳስባቸው የድርጅቱ ባለቤት ወ/ሮ ሳቤላ አባይ ገልፀዋል።
ፎርቹውን እንደዘገበው ማዕከሉ ላለፉት 20 ዓመታት የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ሲያስተዋውቅ የቆየ ተቋም ነው።