ኢሳት (ሚያዚያ 30 ፥ 2009)
በተያዘው ወር የአለም ጤና ድርጅት ሃላፊን ለመምራት በሚደረገው የአባል ሃገራት ምርጫ ብሪታኒያዊው ተወዳዳሪ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድንጋጌ መሰረት የመመረጥ እድላቸው አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ።
ብሪታኒያ በአባልነት ያለችበት የጸጥታው ምክር ቤት ደንብ መሰረት ሃገሪቱ ለአለም ጤና ድርጅት ሃላፊን ከመወከል እንደሚከለክላት ብሪኪንግ ታይም የተሰኘ የጤና መጽሄት ሰኞ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ዘገባ አመልክቷል። ይኸው አለም አቀፍ ድንጋጌ ከሶስቱ የመጨረሻ ተወዳዳሪዎች አንዱ የሆኑትን ዶ/ር ዴቪድ ናባሮን ከተፎካካሪነት ሊያሰናብታቸው እንደሚችል ታውቋል።
የብሪታኒያው ተፎካካሪ ድምፅ አለማግኘት ለኢትዮጵያው ተወዳዳሪ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ዕድልን እንደሚሰጥና ፉክክሩ በዶ/ር ቴዎድሮስና በፓኪስታኗ ተወዳዳሪ ዶ/ር ሳኒያ ኒሽታር መካከል ብቻ እንደሚሆን መጽሄቱ አስነብቧል።
በቅርቡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ለመሆኑ በእጩነት ከቀረቡ አምስት ተፎካካሪዎች መካከል ሁለቱ በቦርድ አባላት ዘንድ አነስተኛ ድምፅን በማግኘት ከፉክክሩ መሰናበታቸው ይታወሳል። ሶስት ተፎካካሪዎች ለመጨረሻ ዙር ያለፉ ሲሆን፣ የብሪታኒያው ተወካይ በጸጥታው ምክር ቤት ድንጋጌ መሰረት በአባላት ዘንድ ድምፅ የማግኘት እድላቸው ያነሰ መሆኑ ተመልክቷል።
የጸጥታው ምክር ቤት ድንጋጌ አባል ሃገራቱ የጤና ድርጅቱን ከመምራት ያግዳል ቢባልም፣ ብሪታኒያዊው ተፎካካሪ ለውድድሩ እንዴት ሊቀርቡ እንዳቻሉ መጽሄቱ ያቀረበው ዝርዝር መረጃ የለም።
በተያዘው ወር የአለም ጤና ድርጅት አባል ሃገራት በሚያካሄዱት ድምፅ የመስጠት ሂደት ቀጣዩን የድርጅቱን ዋና ዳይሬክተር ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። የተለያዩ አለም አቀፍ የጤና አካላት ድርጅቱን የማስተዳደር እድል አግኝታ የማታውቀው አፍሪካ ድርጅቱን የመምራት ተራ እንዲሰጣት ድምፅ እያሰሙ መሆኑም ታውቋል።
የመጨረሻ ድምፅን ለማግኘት የኢትዮጵያና የፓኪስታን ተወካዮች ሰፊ የምረጡኝ ዘመቻን በተለያዩ ሃገራት ዘንድ ሲያካሄዱ መሰንበታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።
የአለም ጤና ድርጅት በቅርቡ በአፍሪካ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ለሆነው የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በቂ ትኩረት አልሰጠም ተብሎ ከፍተኛ ትችት ሲቀርብበት መቆየቱ የሚታወስ ነው።