ብሄራዊ ባንክ 5 የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ከፍተኛ አመራሮችን አነሳ

ኢሳት ዜና (መስከረም 12 ፣ 2008)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አምስት ከፍተኛ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ አመራሮችን ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተገናኘ ዛሬ ረቡዕ ከሃላፊነታቸው አነሳ።

የቀድሞ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታና የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር ዶ/ር አበራ ደሬሳ፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ፣ እንዲሁም ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶች አቶ ቶሎሳ በየነና፣ አቶ አበበ ጥላሁን ከባንኩ አመራርነት መነሳታቸው ታውቋል።

የኦሮሚያ ህብረት ስራ ማህበር ባንክ የአለም አቀፍ ማንኪንግ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ባንታየሁ ከበደም ለአመታት ካገለገሉበት ሃላፊነት መሰናበታቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የብሄራዊ ባንክ እርምጃው ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተገናኘ እንደሆነ ቢገልፅም፣ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአንድ ጊዜ አምስት ከፍተኛ የባንክ አመራሮችን ከሃላፊነት ሲያሰናብት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ድርጊቱ በኦሮሚያ ህብረት ባንክ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ ተሰግቷል።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ የብሄራዊ ባንክ በግል ባንኮች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥሩን እንደሚያደርግ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ይገልጻሉ።

ከሁለት አመት በፊት የብሄራዊ ባንክ ከውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀም ጋር በተገኛኘ የተወሰኑ የባንኩ ሃላፊዎች ከሃላፊነት ማንሳቱ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ረቡዕ የተወሰደው እርምጃም በግል ባንኮች ዘንድ ድንጋጤን መፍጠሩ ታውቋል።

ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ መንግስት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ዘንድ በሁለተኛ ዙር ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለመበደር በዝግጅት ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

በተጠናቀቀው 2007 አም ያጋጠመውን የውጭ ንግድ ማሽቆልቆልና የአንደኛውን ዙር ትራንስፎርሜሽንና የእድገት እቅድ አለመሳካት ተከትሎ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በጣም ዝቅተኛ መሆኑን የመንግስት ባለስልጣናት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ሰአትም ለተወሰኑ ተቋማት ብቻ የውጭ ምንዛሪ እየተሰጠ እንደሚገኝ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።