ታህሳስ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የልደት በዓል በመላው ዓለም እየተከበረ ነው:: ሊቀ-ጳጳስ ቤኔዲክት 16ኛ ለሶሪያ ሰላም ጥሪ ያቀረቡት ዛሬ የፈረንጆች ገናን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ነው።
በቫቲካን ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ፔጥሮስ አደባባይ ቡራኬያቸውን ለመቀበል ለተገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ አማኞች ባስተላለፉት የመልካም ልደት መልዕክት ላይ በተለየ መልኩ ትኩረት ሰጥተው ለሶሪያ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ጥሪ ያቀረቡት ሊቀ-ጳጳሱ፤በሁሉም ወገን ሶሪያውያንም ጠመንጃቸውን በመጣል ለመነጋገርና ለመደራደር ዝግጁ እንዲሆኑ ተማጽነዋል።
<<ደም አፋሳሹ እልቂትና የዜጎች መፈናቀል እንዲገታ እማፀናለሁ>> ሲሉ ተደምጠዋል-ቤኔዲክት 16ኛ።
በ2011 መግቢያ ላይ በተቃዋሚዎች የለውጥ ጥያቄ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በግጭቱ 40,000 ሶሪያውያን ማለቃቸውን አክቲቪስቶችን በመጥቀስ ቢቢሲ አመልክቷል።
ቤኔዲክት 16ኛ ከዚህም ባሻገር በናይጀሪያ በተደጋጋሚ በተከሰተውና ክርስቲያኖችን ኢላማ ባደረገው የሽብርተኞች ድርጊት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ጸሎት ማድረጋቸውን የዜና አውታሩ ዘግቧል።
እንዲሁም የቻይና አዲስ አመራር ሀይማኖቶች ወንድማማች የሆነ ህብረተሰብን ለመፍጠር ለሚያደርጉት ተሳትፎ አክብሮት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት ከተማ በቤተ-ልሔም የተወለደበት የልደት በዓል በመላው ዓለም ላይ በድምቀት ሲከበር ውሏል።
1700 ዓመት ዕድሜ ባላትና ኢየሱስ በተወለደባት በቤተ-ልሔምም በዓሉ በጸሎትና በክርስቲያናዊ ሥነ-ስርዓት በድምቀት ተከብሯል።