ኢሳት (ሚያዚያ 6 ፥ 2009)
በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ቤት ለመግዛት ክፍያን ከፈጸሙ በኋላ ቤቱን ለመረከብ ሲሄዱ ሆቴል ሆኖ እንደጠበቃቸው ተዘገበ። ድርጊቱን የፈጸመው ኬርያ የተባለው ሪል ስቴት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ቢያመራም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይበልጥ አስገራሚ መሆኑ ተመክቷል።
የማምኮ ወረቀት ፋብሪካ ሃላፊ በሆኑ በሼክ መሃመድ አላሙዲ አጎት በአቶ መርዱፍ የተቋቋመው ኬሪያ ሪል ስቴት፣ ከሰባት አመት በፊት ቤት ሰርቼ አስረክባለው ብለው የቤቱን ዋጋ በውጭ ምንዛሬና በኢትዮጵያ ብር ከተቀበሉ በኋላ ደንበኛቻቸው ቤታቸውን ሊረከቡ ሲመጡ ቤታቸው ወደ ሆቴልነት ተቀይሮ እንደጠበቃቸው በሃገር ቤት ጋዜጦች ተዘግቧል።
ሰንደቅ እንደዘገበው ተበዳዮቹ እነ አቶ ዮናስ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት ቢያመለክቱም ሰሚ ማጣቸው ታውቋል። የሰበር ሰሚው ዳኛ የሆኑት አቶ አሊ መሃመድ እና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሸምሱ ሲርጋጋ ህጉ ባለሃብቶችን ስለሚያበረታታ ኬሪያ ሪል ስቴት ድርጅት ለሆቴል አገልግሎት የዋለውን ቤት ለአቶ ዮናስ ሊያስረክብ አይገባም በማለት ውሳኔ ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ሌሎች ግለሰቦቹ የከፈሉትን ገንዘብ ሰበር ፍርድ ቤት እንዲያሰጣቸው ቢጠይቁም የሰበር ዳኞች አንወስንም በማለት ከአምስት አመት ክርክር በኋላ እንደ አዲስ ከታች ፍርድ ቤት እንዲያመለክቱ በማለት ለተጨማሪ መጉላላት መዳረጋቸው ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በተለያየ አገሮች የሚኖሩ ከ40 በላይ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ይርጋለም ሪል ስቴት ከተባለ ድርጅት ጋር ውል በመፈጸም፤ የቤቱን ዋጋ ከ50 በመቶ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የቅድሚያ ክፍያ ከፍለው እንዳጠናቀቁ ቢገልጹም ከሶስት አመት በኋላ ቤቶቻቸውን መረከብ እንዳልቻሉ ገለጹ። በውጭ አገር የሚኖሩ የይርጋለም ሪል ስቴት ደንበኞች ቤቶቻቸውን ቃል በተገባላቸው መሰረት ለመረከብ ባለመቻላቸው በየግዜው ወደ ኢትዮጵያ በመመላለስ ለቤት ኪራይ እና ለሆቴል ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸዋል። የሪል ስቴት ኩባኒያው ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ይርጋለም አሰፋ በበኩላቸው ችግሩ ከኩባኒያው ሳይሆን ባልተጠበቀ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመፈጠሩ ባንኮች የምንዛሪ አቅርቦት ለሪል ስቴት ሊሰጡ ባለመቻላቸው ግንባታው መጓተቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሪል ስቴት ዘርፍ ተዓማኒነት እያጣ እንደሆነ የተናሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ ተዓማኒነት ካጣባቸው ምክኒያቶች መካከል በዘርፉ የተስማሩ አልሚዮች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይዘው ሲሄዱ መንግስት የሚቆጣጠርበት ስረአት አለማበጀቱ እና ግዴለሽ በመሆኑ ነው ሲል ገልጿል። አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ደግሞ የመንግስት ባለስልጣኖች ከቤት አልሚዮች ጋር ድብቅ የጥቅም መጋራት ስላላቸው የህግ አስፈጻሚው አካል በህገወጦች ላይ ለመወሰን እደተቸገረ ይገልጻሉ።