መጋቢት ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እስራኤል ውስጥ የሚኖሩ ቤተ እስራኤላዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸው እንዲመጡላቸው በማለት እሁድ እለት ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ በእየሩሳሌም አካሂደዋል።
ኢትዮጵያዊ ቤተ – እስራኤላዊያኑ በኢትዮጵያ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ምስልን በመያዝ መድልዎ ይቁም፣ ዘረኝነት ይብቃ፣ የሚልና ሌሎችንም መፈክሮች በማንገብ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት በመሄድ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።
ቁጥራቸው በግምት ከሁለት ሽህ በላይ የሚሆኑት ሰላማዊ ሰልፈኞች ለረዥም ዓመታት ተለይተዋቸው ከኖሩት ቤተሰቦቻቸው ጋር ካለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚገናኙበት መንገድ በአፋጣኝ እንዲመቻችላቸው በአጽኖት ጠይቀዋል።
ከሰልፈኞቹ አንዱ የሆኑት አንተዬ ቸኮል ወንድማቸውና አባታቸው ለሃያ ዓመታት በስደተኞች ቢሮ መጉላላታቸውን ገልፀው ”ከኢትዮጵያ ለሚመጡ ቤተ-እስራኤላዊያን እንዲጉላሉ እየተደረገ ከአሜሪካና ከሩሲያ ለሚመጡት ግን ይፈቀዳል።ይህም በቀላሉ ዘረኝነት ነው!” ሲሉ ለኤኤፍፒ መግለጻቸውን ጄሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።