(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 24/2010)
በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ላይ የተጀመረው ተቃውሞ አሁንም መቀጠሉ ተገለጸ።
ዛሬ ባሻምቡ ወለጋ በኦሮምኛና በአማርኛ የተጻፉ መፈክሮችን ይዘው አደባባይ የወጡት ሰልፈኞች የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ አንድ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኦሮሚያ ክልል መሪዎች ወደ ባህርዳር ያደረጉት ጉዞና የሁለቱን ክልሎች ትብብር መርህ አልባ ሲል ማውገዙ ይታወሳል።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ ትብብሩን ባጣጣለ ማግስት ግን በአማርኛ የተጻፈ መፈክር ጭምር ይዘው በአማርኛም የተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰሙት የሻምቡ ወለጋ ነዋሪዎች ናቸው።
ለመግለጫው የሰጡት አጸፋ ስለመሆኑም የተለያዩ አስተያየቶች በመቅረብ ላይ ናቸው።
“አንድ ነን መቼም አንለያይም” የሚል መፈክር በማለት የተቅውሞ ድምጽእቸውን ሲያሰሙ በምስልና በድምጽ የሚያዩትና የሚደመጡት የሻምቡ ወለጋ ነዋሪዎች “የኦሮሞ ጠላት የአማራ ጠላት ነው” “የአማራ ጠላት የኦሮሞ ጠላት ነው”ሲሉም በምስል በተደገፈው መረጃ ላይ ታይተዋል።
የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን ከመጣበት ከ1983 ወዲህ በሁለቱ ትላልቅ ብሔረሰቦች መካከል ጥርጣሬንና ግጭትን የሚጋብዙ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ መቆየታቸው ይታወሳል።
የኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መፋፋሙን ተከትሎ በጎንደር ከፍተኛ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በታየበት ወቅት ለኦሮሞ ወጣቶች የተሰጠው የአጋርነት ድጋፍ የሕወሃት ባለስልጣናትን እንዳላስደሰተም ማስታወስ ተችሏል።
አሁን የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ እሳትና ጭድ እንዴት ይተባበራል ይህም ስርአቱ በአግባቡ ባለመስራቱ የተከተለ ነው ማለታቸው አይዘነጋም።
አቶ ለማ መገርሳ የኦህዴድ ሊቀመንበር እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት መሆናቸውን ተከትሎ በሁለቱ ክልሎች መካከል ትብብሮች ተጠናክረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ባህርዳር ሄደው የጋራ ጉባኤ ማካሄዳቸውም አይዘነጋም።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመግለጫው ይህንን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መርህ አልባ ሲል ማጣጣሉ ይታወቃል።
የሻምቡ ተቃውሞም ይህንን ተከትሎ መካሄዱም ለመግለጫው የተሰጠ የተቃውሞ አጸፋ ስለሆነም አስተያየት ሰጭዎች በመጻፍ ላይ ናቸው።