ባለፉት 4 ወራት 7 የደህንነት አባላት ተገደሉ

ኢሳት (ሰኔ 9 ፥ 2008)

ባለፉት 4 ወራት 7 የኢትዮጵያ መንግስት የደህንነት ሰራተኞችንና አስተባባሪዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአልሞ ተኳሾች መገደላቸውን የኢሳት ምንጮች ገለጹ። ዘውዱ ተከለማሪያም፣ ሲሳይ እና ኤሊያስ የተባሉትን የደህንነት አስተባባሪዎችን ጨምሮ 7 የደህንነት ሰራተኞች በሃረር፣ አዳማና ደብረዘይት ተገለዋል።

በተለይም በሶማሊ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ደህንነት መዋቅር አስተባባሪ ወይንም ኢንተለጀንስ ኦፕሬሽን ኮኦርዲኔተር የሆኑት ሶስቱ የህወሃት አባላት መገደል በሶማሊያ ከአልሻባብ ጋር በሚደረገው ውጊያ ላይ ጉልህ  ተፅዕኖ እንደሚኖረውም ተመልክቷል።

ዘውዱ ተከለማርያም በተለዋጭ ስሙ ሙሃመድ ኡመር፣ ሲሳይ በተለዋጭ ስሙ ካሊድ ኡስማን፣ ኤሊያስ በተለዋጭ ስሙ ተኽላይ ወልደጊዮርጊስ ሃረር አዳማና ደብረዘይት ባልታወቁ አልሞ ተኳሾች ባለፉት ሁለት ወራት መገደል ከፍተኛ ስጋር አስከትሏል። እነዚህ ሶስቱ የህወሃት አባላት በም/ጠ/ሚኒስትር ደብረጽዮን ስር ሆነ በአጠቃላይ የሶማሊያን የደህንነት ስራ ስያከናውኑ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።

ከእነዚህ የደህንነት አስተባባሪዎች በተጨማሪ፣ ተመስገን፣ ካሳ ግደይ፣ ሰዒድ ሽሬና ጎቻ የተባሉ የደህንነት አባላት ባለፉት አራት ወራት መገደላቸውም በደህንነት መዋቅር ውስጥ ስጋትን አስከትሏል።

ሟቾቹ የህወሃት አባላት በመሆናቸው፣ የሌላ ብሄረሰብ አባላት የሆኑ የደህንነት ሰራተኞች ተጠርጥረው የታሰሩ ሲሆን፣ ከግድያው ጋር በተያያዘ የውጭ መንግስት እጅ አለበት የሚል ስጋት አስከትሏል።