ባለፉት አምስት ወራት የውጭ ንግድ ገቢ የ700 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ጉድለት ማስመዝገቡን የንግድ ሚኒስቴር ገለጸ

ኢሳት (ጥር 17 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ንግድ ገቢ ባለፉት አምስት ወራቶች የ700 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ጉድለት ማስመዝገቡን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሃገሪቱ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ከውጭ ንግድ ገቢ ወደ 1.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት እቅድን ይዛ የነበረ ቢሆንም፣ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ግን ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የሃገሪቱ 70 በመቶ አካባቢ ንግድ በግብርና ምርቶች ላይ መመርኮዙን ያስታወቀው የንግድ ሚኒስቴር በዚሁ ዘር የታየው የጥራትና የአለም አቀፍ የዋጋ መዋዠቅ በውጭ ንግድ ገቢው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አመልክቷል።

ከቀናት በፊት ሚኒስቴር በኢንዱስትሪ የማኑፋክቸሪንግ ዘፍ ተመሳሳይ የገቢ መቀነስ መመዝገቡን ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ወራቶች ብቻ የተመዘገበው የውጭ ንግድ ገቢ ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑ ታውቋል።

የሃገሪቱ የውጭ ንግድ ገቢ እየቀነሰ መምጣት በውጭ ምንዛሪ ክምችትና በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሚገኝ የአለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የልማት አጋር የሆነው ባንኩ መንግስት ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ ሲል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል። የአለም ባንክ የኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብ ብር ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ቢጠይቅም መንግስት እርምጃው ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል ሲል ሃሳቡን እንደማይቀበል አስታውቋል።

ይሁንና መንግስት አጋጥሞት ያለውን የፋይናንስ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ሲል የቦንድ ሽያጭ እንዲያከናውን የወሰነ ሲሆን፣ የባህረ ሰላጤ ሃገራትም ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ እንዲያስቀምጡ በመደረግ ላይ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው ለሽያጭ ሊቀርብ የተዘጋጀው 27 ቢሊዮን ብር የቦንድ ሽያጭ የዋጋ ግሽበት ያባብሳል ሲሉ አሳስበዋል።

ሃገሪቱ አጋጥሟት ያለውን የውጭ ንግድ መዋዠቅ ለመታደግ በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች የውጭ ገበያ ለማፈላለግ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር አክሎ አስታውቋል።

የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አያና ዘውዴ ሃገሪቱ ያጋጠማት የውጭ ንግድ መቀዛቀስ ለመፍታት ምርቶችን በብዛት በጥራት በመላክ አገሪቱ የምትፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።