ሐምሌ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሁለተኛውን የኢህአዴግ መንግስት የ5 አመታት የመከላከያ ሰራዊት እቅድ በተመለከተ በቤተመንግስት በተካሄደው ስብሰባ ላይ ኢህአዴግ አሁን ያለውን ወታደራዊ አቅምና በሚቀጥሉት አምስት አመታት የሚያስፈልጉትን የጦር መሳሪያዎች በጄ/ል ሳሞራ የኑስ በኩል ዘርዝሮ ያቀረበ ሲሆን፣ በዚህ ሪፖርት ወቅት ባለፉት 5 አመታት ወደ ቻይና ፣ ኮሪያ ፣ ጃፓን እና እስራኤል ለወታደራዊ ስልጠና ከተላኩት 714 ወታደራዊ ሰልጣኞች መካካል ስልጠናውን አጠናቀው ወደ አገራቸው የተላኩት 43 በመቶ ብቻ ናቸው። ወታደራዊ ክዳት የስርአቱ ፈተና መሆኑ ተገልጿል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ ከፍተኛ መኮንኖችን ያነጋገረው የባህር ሃይል ይመስረት የሚለው ሃሳብ ነው። አመራሮቹ ስልጠናውን ከጀቡቲ መንግስት ጋር በማቀናጀት መምራት ይቻላል የሚል ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ አዲስ በሚጀመረው የባህር ሃይል ስልጠናም ኤስ ኤች-2ጀ ሲስፕሪት ፤ ኤስኤ-342 ኤል ጋዚሊ ፤ ዋስትላንድ ሲ ኪንግ ኤምኬ 47 በሚባሉት ዘርፎች ስልጠና እንዲሰጥባቸው ውሳኔ ተላልፏል።
በኬሚካል የቀላል የጦር መሳሪያዎች ምርምር ሙከራ ቢደረግም፣ አገሪቷ አጋዥ አገር በማጣቷ ወደ ስራው ልትገባ አልቻለችም የሚል ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ከቻይና ጋር በመጎዳኘት ስራ ለመጀመር ማቀዷ ታውቋል። ነርቭን የሚጎዳና የሳይናይድ ጋዝን ለማምረት ዲዛይን መጠናቀቁ ተነግሯል።
የሰራዊቱ ድክመት ተብለው ከቀረቡት ችግሮች መካከል በአጠቃላይ ለማንኛውም ጦርነት የተዘጋጀ ሃይል አለመኖር ፤ አብዛኛው ወታደራዊ ሃይል የጦር የነፍስ ወከፍ ክላሽ መሳሪያዎች ለይ የተገደበ መሆን ፤ ሰራዊቱ በስርአቱ ደስተኛ አለመሆን፣ በፍላጎት መርጦ ሳይሆን ፤ ኑሮውን የሚሸፍንበት አማራጭ በመጣት የሚደራጅ ሰራዊት መሆን የሚሉት ይገኙበታል።
ከሌሎች ወታደራዊ ጀኔራሎች በተሰጠ አሰተያየት ደግሞ የሰራዊቱ አባላት በአስቸጋሪ የአየር ፀባይና በፈታኝ ጦርነቶች የመሳተፍ አቅማቸው አነስተኛ ነው ተብሎአል።
“የተቀናጁ መሳሪያዎና የጥምር ውጊያ አቅም አነስተኛ መሆን፤ የሳተላይተ መረጃ መጠቅም ላይ ያለው አቅም ውስንነት ፤ ለኤሌክትሮኒክ ጦርነት ዝግጁነት የሌለ መሆኑ ፤ በኤርትራ፣ ሶማሌ እና በሱዳን በተካሄዱ ውጊያዎች የጦርነት ልምድ ወስዶ የራሳችንን ውጊያ ልምድ አለማዳበር ” የሚሉ አስተያየቶችም ተሰንዝረዋል፡፡
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የመለስን ወታደራዊ መሃንዲስነት አንስተው በሰጡት አስተያየት ” ባለፉት አመታት ትንስፎርሜሽን አልነበረም ፤ እድገት ግን ነበረ” ያሉ ሲሆን ፣ ‘ በጦር ሃይሉ ብቻ ትንስፎርሜሽን ማምጣት የምንችልበት ደረጃ ላይ ነን” በማለት ፣ ሰው አልባ አውሮፕላን ለመስራት የተደረገውን ጥረት እና መከላከያ ወደ ንግድ ስራ ገብቶ ያሳየውን ትርፋማነት ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢህአዴግ ያለውን የጦር መሳሪያ ዝርዝር ባለፈው የዜና ዘገባችን ማቅረባችን ይታወሳል። መከላከያ ሰራዊት በሚቀጥሉት አምስት አመታት ለመግዛት ያሰባቸውን የጦር መሳሪያዎችና ተዋጊ ጄቶች አይነት በነገው ዘገባ ይዘን እንቀርባለን።
በሌላ ዜና ደግሞ በደቡብ ክልል ሰራዊት አባላትን ለመመልመል የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ። የአካባባው ወኪላችን እንደገለጸው በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች የወታደራዊ ቅጥር ማስታወቂያዎች ቢለጠፉም፣ ተመዝጋቢ በመጥፋቱ በየቀበሌው ኮታ መጣሉን ተናግረዋል። ይሁን እንጅ ይህን ኮታ የሞሞላ የሰው ሃይል በመጥፋቱ፣ የቀበሌ አመራሮች ለሙያ ስልጠና እና ወደ አረብ አገር ለመሄድ በሚል ወጣቶቹን መመዝገብ ጀምረዋል።