የካቲት ፳፪ ( ሃያ ሁለት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል የከተማ ታክሲዎችና ባጃጆች ላይ የወጣውና ከፍተኛ ተቃውሞ በማስነሳት ከሶስት ቀን በላይ የስራማቆም አድማ በማድረግ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታገድ ተደርጎ የነበረው ህግ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን በመጀመሩ ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
ታክሲዎችና ባጃጆች ሰሞኑን በተጀመረው በአንድ ምድብ ብቻ እንዲሰሩና ወደ የትኛውም የከተማዋ አካባቢ ለግል ጉዳይም ሆነ በኮንትራት እንዳይነቀሳቀሱ መታገዳቸው በተገልጋዩና በአሽከርካሪዎች ላይ ችግር መፍጠሩን የሚናገሩት አሽከርካሪዎች ከአስር በላይ ተሸከርካሪዎች በቤተሰብ ችግር ምክንያት ወደተለያዩ የህክምና ቦታዎች በመጓዛቸው አምስት አምስት መቶ ብር መቀጣታቸው አግባብ እንዳልሆነ ቅሬታ አቅራቢዎች ተናግረዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢ አሽከርካሪዎች እንደሚናገሩት የታክሲና ባጃጆች ስምሪት በየማህበራቸው በመሆኑና የባጃጆችን ቁጥር ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ተሳፋሪ በብዛት በሌለባቸው መስመሮች ከተገቢው በላይ ባጃጆች ተመድበው ቀኑን ሙሉ ያለስራ ወረፋ በመጠበቅ የሚውሉ አሽከርካሪዎች አሉ፡፡
ከአሁን በፊት ተሳፋሪ በሚበዙባቸው መስመሮች ባጃጆች በፈቃዳቸው ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር የሚገልጹት አሽከርካሪዎች ዛሬ በአዲሱ ህግ መሰረት በተደረገው ምደባ ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት በመኖሩ በርካታ የተሳፋሪዎች ወረፋ ይታያል፡፡