ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2009)
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 ቻይናን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ከ 3ሺ በሚበልጡ ላይ የሞት ቅጣት መፈጸማቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ማክስኞ ይፋ አደረገ።
ቻይና በአለማችን ካሉ ሃገራት የሞት ቅጣቱን በብዛት በመፈጸም በግንባር ቀደምትነት የተቀመጠች ሲሆን፣ ኢራን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራቅ እና ፓኪስታን ከሁለት እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘዋል።
ባለፈው የፈረንጆች አመት ከ3ሺ በላይ ሰዎች ላይ ተፈጻሚ ከሆነው የሞት ቅጣት 90 በመቶ የሚሆነው በአምስት ሃገራት መካሄዱም ታውቋል።
በአጠቃላይ በ55 ሃገራት የሞት ቅጣቱ ተፈጻሚ እንደነበር ያወሳው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የባለፈው አመት ቁጥር ከ2015 አም ጋር ሲነጻጸር የ56 በመቶ ብልጫ ማስመዝገቡን ለመረዳት ተችሏል።
የሞት ቅጣቱን በመፈጸም ግንባት ቀደም ሃገር የሆነችው ቻይና ከአንድ ሺ በላይ ዜጎቿን ለግድያ በማብቃት በ23 ሃገራት ከተፈጸሙ ተመሳሳይ ቅጣቶች አብዛኛውን ድርሻ እንደያዘች ቪኦኤ እንግሊዝኛው ክፍል ዘግቧል። ይሁንና፣ ሃገሪቱ በሞት የምትቀጣቸው ሰዎች ቁጥር በአግባቡ የማትገልፅ በመሆኑ ትክክለኛ ቁጥሩን ማወቅ እንዳልተቻለ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ አመልክቷል።
በአለማችን እንደ ቻይና በምስጢራዊ መንገድና በብዛት በሰዎች ላይ የሞት ቅጣትን የሚፈጽም ሃገር የለም ሲሉ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የኤዥያ ሃገራት ሃላፊ የሆኑት ኒኮላስ ቢኬሊን ለዜና ወኪሉ ገልጸዋል።
ተመሳሳይ ድርጊትን በመፈጸም የምትታወቀው አሜሪካ በ20 አመት ታሪክ ውስጥ በ20 ሰዎች ላይ ብቻ የሞት ቅጣትን ተግባራዊ በማድረግ ግንባር ቀደም ተብለው ከተፈረጁ አምስት ሃገራት ተርታ መውጣቷም ታውቋል።
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2016 አሜሪካ በሰባተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን አፍሪካዊቷ ግብፅ ደግሞ ስድስተኛ ደረጃን ይዛለች።
በአሜሪካ የተፈጸሙት የሞት ቅጣቶች በአብዛኛው በጆርጂያና ቴክሳስ ግዛቶች የተካሄደ መሆኑን ያወሳው አምነስቲ ኢንተርናሽናል 19 የሃገሪቱ ግዛቶች የሞት ቅጣት እንዲቀር ህግ ማውታጣቸውን በሪፖርቱ አስፍሯል። አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሞት ቅጣትን እንደሚደግፉ ቢገልጹም፣ በሃገሪቱ የሞት ቅጣትን የሚደግፉ አካላት ወደ 49 በመቶ ማሽቆልቆሉን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ገልጿል።