ጥቅምት ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአዲስ አበባ ከተማ የተመሰረተበትን 125ኛ ዓመት ክብረ በዓል በማስመልከት ባለውለታዎችን ለማመስገን እና ዕውቅና ለመስጠት በሚል የታሰበው የሸልማት ፕሮግራም ከወዲሁ እየተተቸ ነው፡፡
የአስተዳደሩ በዓል አዘጋጅ ኮሚቴ በውድድር እና ያለውድድር ባለውለታ የሆኑ ሰዎችን ለመሸለም ያቀደ ሲሆን ሸልማቱን ለመስጠት የተቀመጡት መስፈርቶች በአመዛኙ ፓለቲካዊ መሆናቸው ትችትን አስከትሎበታል፡፡
በእቅዱ መሰረት ባለፉት ዓመታት በልማት፣በሥራ ፈጠራ፣ በዴሞክራሲ፣በመልካም አስተዳደር፣በፍትህ፣ በጸጥታ እና በመሳሰሉ ዘርፎች የላቀ አስተዋጽዖ ያደረጉ ሰዎችን ለመሸለም መታቀዱን ምንጫችን አስታውሶ እነዚህ ነጥቦች የኢህአዴግን ዓላማ ከማሳካት አንጻር ብቻ የሚታዩ መሆናቸው የማይቀር ነው ብለዋል፡፡
ለከተማዋ ዕድገትና ልማት በተለያዩ ወቅቶች ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ ግን በራሳቸው የፖለቲካ አቋም ምክንያት አሁን ያለውን ሥርዓት የማይደግፉ መኖራቸውን ምንጮቹ አስታውሰው ይሁን እንጂ ሰዎቹ በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት በክብር የሚመሰገኑበት ሁኔታ መኖሩ ጉዳይ ከወዲሁ አጠራጣሪ መሆኑ የሸልማቱን ፋይዳ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ከቶታል፡፡
የስራ ጊዜውን ሊያጠናቅቅ ከስድስት ወራት ያነሰ ጊዜ ብቻ የቀረው የኩማ አስተዳደር የአዲስአበባን 125ኛ ዓመት አከብራለሁ በሚል ደፋ ቀና ማለት ከጀመረ ወራትን ቢያስቆጥርም በሕዝቡም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን በተለይም (በግሉ) ተገቢውን ትኩረት ሳይገኝ ቀርቷል፡፡
አስተዳደሩ 125ኛ ዓመት አከብራለሁ ብሎ ከያዘው ሩጫ ይልቅ እስከ ወረዳ ባለው መንግስታዊ መዋቅር በስፋት የሚታየው የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮች እንዲፈቱለት፣ከሕዝብና ከመንግስት ዘርፈው ከገቢ በላይ ሐብትና ንብረት ያፈሩ ሰዎች በሕግ እንዲጠየቁለት በመወትወት ላይ ይገኛል፡፡