ባህርዳር ውስጥ በእግረኞች ማቋረጫ መንገድ ላይ አንድን ወጣት ገጭቶ የገደለው ባለስልጣን ከተለቀቀ በሁዋላ መልሶ ታሰረ

መጋቢት ፳፩ (ሃያ አንድ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሃይለኛ የስካር መንፈስ ውስጥ ሆኖ ሲያሸከረክር የነበረው የአማራ ክልል አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አገኘሁ ተሻገር በእግረኞች ማቋረጫ መንገድ ወይም “ዜብራ ክሮስ” ላይ ጋሻው የተባለውን ወጣት ገጭቶ ከገደለው በሁዋላ፣ በእለቱ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ቢወሰድም በማግስቱ የተለቀቀ ሲሆን፣ ኢሳት ዜናውን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ግን ተመልሶ እንዲታሰር መደረጉን ምንጮች ገልጸዋል።
ድርጊቱ የከተማው ህዝብ መነጋገሪያ ርእስ መሆኑን የተረዱት ፖሊሶች ባለስልጣኑ ለጊዜው በእስር ቤት እንዲቆይ አድርገውታል። ፖሊሶች ሃዘን ቤት ድረስ በመሄድ አደጋው በተፈጸመበት እለት ከነበሩ ወጣቶች መካከል አንዱን ቃሉን እንዲሰጥ የነገሩት ሲሆን፣ የቃል አሰጣጡ ሂደት ፈታኝ እንደሚሆንበትም አስጠንቅቀውታል።
የአይን እማኞች እንደሚሉት ትሪፊክ ፖሊሶች ሆን ብለው አደጋው ከደረሰበት ከእግረኛ ማቋረጫው መንገድ 50 ሜትር ባለ ርቀት ላይ ሲለኩ መታየታቸውን ባለስልጣኑ በወንጀል እንዳይከሰስ ለማድርግ ነው። አንድ አሽከርካሪ ሰው ገጭቶ ቢገድል ከ15 እስከ 25 ዓመታት እንደሚታሰር ህግ ወጥቶ እያለ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚፈጅ መኪና በስካር መንፈስ እያሽከረከሩ ሰዎችን የሚገድሉ ባለስልጣናትን ምሽት ላይ አስሮ ጠዋት ላይ መልቀቅ በአገሪቱ ያለውን የፍትህ ስርዓት መበላሸት ያሳያል ይላሉ።
ነዋሪዎቹ የፖሊሶች ሁኔታ ባለስልጣኑ ቶሎ ይለቀቃል ብለው እንዲያምኑ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ።