ኢሳት ( ግንቦት 4 ፥ 2009)
የብሪታኒያው የማሰራጫ ጣቢያ ቢቢሲ ሶስት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ጨምሮ በስድስት ቋንቋዎች ለሚጀምረው የራዲዮ ስርጭት በኬኒያ አዲስ ቢሮ እንደሚከፍት አርብ አስታወቀ።
በኬንያ መዲና ናይሮቤ ለሚከፈተው ለዚሁ ቢሮ 10 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተመድቧል። ስቱዲዮው ለ250 ሰዎች የስራ እድልን እንደሚፈጥር የቢቢሲ ተወካዮች ገልጸዋል።
የብሪታኒያ መንግስት የማሰራጫ ጣቢያው ለሚጀምረው አዲስ ስርጭት በየአመቱ 85 ሚሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ እንደሚመደብ ባለፈው አመት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በኬንያ በሚቋቋመው በዚሁ አዲስ ዘመናዊ ስቱዲዮ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ እና በትግርኛ ቋንቋዎች የተለያዩ ዝግጅቶች ይቀርባሉ ተብሏል። ተመሳሳይ ስርጭቶች በሩሲያ ሰሜን ኮሪያና በመካከለኛው ምስራቅ እንደሚቀርብ ታውቋል።
የብሪታኒያ ማሰራጫ ጣቢያ ቢቢሲ አዲስ ስርጭት እንዲደርስባቸው የተመረጡት ሃገራት የሰብዓዊ መብት መከበርና የዴሞክራሲ ስርዓት ችግር ያለባቸው መሆኑን ይገልጻል። የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ግን የማሰራጫ ጣቢያው ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ መፈረጁ ተገቢ አይደለም ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
የማሰራጫ ጣቢያው በአዲስ መልክ በሚጀምረው በዚሁ ስርጭት በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሩሲያ፣ ሰሜን ኮሪያና፣ የመካከለኛ ምስራቅ ሃገራት 500 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች መረጃ ለማቅረብ እቅድ እንዳለው ገልጿል።
የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በሃገራቸው ለሚከፈተው አዲስ የቢቢሲ ቢሮ ድጋፍ እንደሚያደርጉና ደስተኛ መሆናቸውን አርብ አስታውቀዋል።
የቢቢሲ የአፍሪካ አዘጋጅ ሰለሞን ሙገራ በናሮቢ የሚከፈተው አዲስ ቢሮ ከስርጭቱ በተጨማሪ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ እንደሚሰጥ ለፕሬዚደንቱ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከሚሰራጩት የራዲዮ ፕሮግራሞች በተጨማሪ ቢቢሲ በሶማሊያ ህንድና ናይጀሪያ እንዲሁም ታይላንድ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደሚጀምር ለመረዳት ተችሏል።
የማስረጫ ጣቢያው ዳይሬክተር ጀኔራል የሆኑት ቶኒ ሃል አዲስ የጀመሩት ፕሮግራም ነጻና ገለልተኛ የሆኑ መረጃዎችን ለማቅረብ ያለሙ መሆናቸውን ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል። የብሪታኒያ መንግስት በበኩሉ ለአዲሱ ስርጭት የሰጠው ገንዘብ ድጋፍ በየሁለቱ አመት የሚታደስ መሆኑ ገልጿል።