ኢሳት (ሰኔ 21 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተከትሎ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ቢሮውን በአዲስ አበባ በመክፈት ብድርን ከመንግስትና ለግል ተቋማት ለማቅረብ የሚያስችለውን ስምምነት ፈጸመ።
በአለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ የሆነው ይኸው ባንክ ቅርንጫፍ ቢሮውን በኢትዮጵያ በመክፈት ብድርን ማቅረብ እንደሚጀምር ታውቋል።
ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ የቱርኩ ዚሪት ባንክ ከወራት በፊት ከሃገር ውስጥ ብድርን ከማቅረብ ስምምነት የፈጸመ ሲሆን መንግስት ከኬንያ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች የባንክ ተቋማት ጋር ድርድር እያካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የአፍሪካ ካሪቢያንንና ፓሲፊክ አገራት ምክትል ፕሬዚደንት ፒም ባንባሌኮም ባንኩ በኢትዮጵያ ቁልፍ ለሆኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የፋይናንስ አቅርቦትን እንደሚያደርግ ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል።
ባንኩ ለመንግስት ከሚያቀርበው የብድር ድጋፍ በተጨማሪ ለግል ተቋማት ተመሳሳይ የፋይናንስ አቅርቦትን እንደሚያደርግ የባንኩ ተወካይ ገልጸዋል።
ይሁንና፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ምን ያህል ገንዘብ ለመንግስት በብድር ለማቅረብ እቅድ እንደያዘ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን ባንኩ ቅርንጫፍ ቢሮውን እንዲከፍት ለአመታት የቆየ ድርድር ሲካሄድ መቆየቱን ለመረዳት ተችሏል።
የህብረቱ ኢንቨስትመንት ባንክ ከ27 የአውሮፓ ሃገራት የገንዘብ ድጋፍ የሚቀርብለት ሲሆን፣ ከተለያዩ ሃገራት ብድርን በመስጠት በየአመቱ በቢሊዮን ዩሮ የሚቆጠር ገንዘብ በማቅረብ ላይ መሆኑን ከባንኩ ድረገጽ ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው አመት የቦንድ ሽያጭን በማካሄድ ብድር ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም በሂደቱ የሚፈለገውን የገንዘብ መጠን አለመገኘቱ ይታወቃል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው የቦንድ ሽያጭ ሊገኝ የታሰበው ገንዘብ ከፍተኛ ብድር የሚከፈልበት በመሆኑ መንግስት ሌላ አማራጭን ለማየት በመወሰን ከተለያዩ ባንኮች ፈቃድን በመስጠት በሃገር ውስጥ ወኪል እንዲከፍቱ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት የሃገሪቱ የባንክ አገልግሎት ከውጭ ኩባንያዎች ክፍት አይደረግም ሲሉ በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።