ኢሳት (ታህሳስ 25 ፥ 2009)
በሶማሊያ ተሰማርቶ በሚገኘው የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ልዑክ ስር ሰራዊቷን አሰማርታ የምትገኘው ብሩንዲ የአፍሪካ ህብረት ወታደሮቿ ክፍያ ባለመፈጸሙ በቀጣዩ ወር ከሶማሊያ ጠቅልላ እንደምትወጣ አስታወቀች።
የሃገሪቱ ባለስልጣናት ወደ 5ሺ 432 አካባቢ የሚጠጉ የብሩንዲ የሰላም አስከባሪ አባላት ለአንድ አመት ያህል ምንም ክፍያ ሳይፈጸምላቸው መቆየቱ ተስፋ መቁረጥ እንዳሳደረባቸው ይፋ ማድረጋቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
በሶማሊያ ተሰማርቶ ለሚገኘው የህብረቱ የሰላም አስከባሪ ሃይል ከፍተኛ ድርሻ ያለውን ሰራዊት አሰማርታ የምትገኘው ሃገሪቱ ወታደቿን ለሰላም አስከባሪነት ለማዘጋጀትና ወደ ሶማሊያ ለማጓጓዝ ከፍተኛ ገንዘብ ወጭ እንዳደረገች የብሩንዲው ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ አስታውቀዋል።
ከአፍሪካ ህብረት ጋር በወታደሮቹ ጥቅማጥቅም ዙሪያ መግባት ቢደርስም ህብረቱ ቃሉን ሊጠብቅ አለመቻሉ እጅጉን የሚያሳዝን ድርጊት ነው ሲሉ ፕሬዚደንቱ ገልጿል።
የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ልዑክ እስከቀጣዩ ወር ድረስ ለወታደሮቹ ውዝፍ ክፍያን መፈጸም ካልጀመረ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ወደሃገራቸው መመለስ እንደሚጀምሩ የብሩንዲው ፕሬዚደንት አስረድተዋል።
ህብረቱ ሃገሪቱ ላቀረበችው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ለህብረቱ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየው የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ወር ሳይሰጥ የቆየውን የገንዘብ ድጋፍ መልቀቁን ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
ከብሩንዲ በተጨማሪ ኬንያ የሰላም አስከባሪ አባላቷን ከሶማሊያ ለማስወጣት ዕቅድ እንዳላት በቅርቡ ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ በፋይናንስ እጥረት ውስጥ ይገኛል የተባለው የአፍሪካን የሰላም አስከባሪ ሃይል አልሸባብ እያደረሰ ያለውን ጥቃት የመቋቋም አቅሙም እየቀነሰ መምጣቱ ይነገራል።
ከወራት በፊት ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ እና በተናጠል ተሰማርተው የነበሩ ወታደሮቿን ከሶማሊያ ስታስወጣ መቆየቷ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ወታደሮቹ መውጣትን ተከትሎም አልሸባብ የተሰኘው የሃገሪቱ ታጣቂ ሃይል በርካታ ቁልፍ የተባሉ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያዎችንና ከተሞችን ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ከሶማሊያ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።