ጥር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ወደዓረብ አገራት ዜጎች የሚያደርጉት ጉዞ ከ2003 ዓ.ም በኋላ በአስደንጋጭ መልኩ ከ4ሺህ ወደ 198 ሺህ
ማደጉን ዶ/ር ዘሪሁን ከበደ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ይፋ አደረጉ፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ለንባብ በበቃው “ዘመን” ከተባለው መንግስታዊ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፤
በ2002 ዓ.ም ሚኒስቴር መ/ቤቱ መሰረታዊ የሥራ ሂደት ጥናት አጥንቶ ተግባራዊ ሲደርግ ከ3-5 ሺህ ሰዎች በዓመት ሊጓዙ ይችላሉ የሚል ስሌት እንደነበረው፣ ነገር ግን በዓመቱ መጨረሻ 12ሺህ ሰዎች መጓዛቸውን ተናግረዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም ይህ ቁጥር ወደ 42 ሺህ በዓመት ማደጉን፣ በ2004 ደግሞ 198 ሺህ 600 ፣በ2005 ዓ.ም ደግሞ ወደ 180 ሺህ 200 ማሻቀቡን አስታውቀዋል፡፡
እነዚህ ወገኖች ሚኒስቴር መ/ቤታቸው በሚያውቀው ሕጋዊ መስመር የተጓዙ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶ/ሩ በህገወጥ መንገድ የሚጓዙት ቁጥራቸው እጥፍ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡ ወደዓረብ አገራት የሚጓዙ ሰዎች ቁጥር ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ያመኑት ሚኒስትር ዴኤታው የዚህ ምክንያቱ በሕጋዊ መንገድ መጓዝ መቻሉ መሆኑን ይናገሩ እንጂ ሌሎች ወገኖች ስርኣቱ ለዜጎች በአገር ውስጥ በቂ ስራ ዕድል መፍጠር ካለመቻሉ ጋር ተያያዘ መሆኑን ሲያስረዱ መቆየታቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ዶ/ር ዘሪሁን በዚሁ ቃለምልልሳቸው በሕገወጥ መንገድ የሚደረገውን የሰዎች ዝውውር መ/ቤታቸው ለመከላከል እንደሚሰራ አስታውሰው ነገር ግን የነበረው የቅንጅት ስራ ደካማ በመሆኑ ውጤታማ እንዳልነበር አምነዋል፡፡
ከሳዑዲ ተመላሾች ቁጥር በተመለከተም ሲጀመር በመንግስት በኩል ከ23 እስከ 28 ሺህ ይሆናሉ የሚል ግምት
እንደነበረ አስታውሰው ነገር ግን በተጨባጭ 141ሺህ 357 ዜጎች ሊመለሱ መቻላቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ወደዓረብ አገራት ለስራ የሚደረግ የውጪ አገር ጉዞ መታገዱን፣ ሕጎችንና አደረጃጀቶችን የማስተካከል ስራዎች በሚኒስቴሩ በኩል እየተከናወነ መሆኑን፣ ወደፊት በሚተገበረው ሕግ ያልሰለጠኑ ሰዎች ወደዓረብ አገራት እንደማይሄዱ አስታውቀዋል፡፡