ታህሳስ 25 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-በ3 ቁጥር ማዞሪያ ቶታል አካባቢ የሚገኘው የአወሊያ ቁጥር 2 ት/ት ቤት ተማሪዎች በትላንትናው ቀን ማክሰኞ በ እስላማዊ ምክር ቤት ወይም መጅሊስ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰሙ፡፡
ተማሪዎቹ ቀኑን ሙሉ የዋለ ተቃውሞ ሊያሰሙ የቻሉበት ምክንያት፤ መጅሊሱ የአረብኛ መምህሮችን ከትምህርት ቤቱ በማባረሩና፤ በምትኩ በራሳቸው ያሰለጠኗቸውንና የአሕባህሽ ተከታይ የሆኑትን በማሰማራት ተማሪዎቹን ከእስልምና ለማስወጣት በማሰባቸው ነው።
ተማሪዋቹ የአህባሽን አመለካከት ፈጽሞ እንደማይቀበሉት፤ መጅሊሱ የቅጥር ግቢውን ዘበኞች ሳይቀር ስልጠና ብሎ የት እንደወሰዳቸው እንደማይታወቅ ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ ከፌደራል የመጡ በርካታ ፖሊሶች ግቢውን በማጠር አንድም ተማሪ ከግቢው እንዳይወጣ አፍነዋቸዋል፤
ህብረተሰቡም ተቃውሞውን እንዳይመለከት የግቢውን አጥር በጨርቅ ሳይቀር ሸፍነውት ነበር፡፡
ፖሊሶቹ ተማሪዎቹን አፍሰው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ካስገቧቸው በኃላ ከከባድ ማስፈራሪያ በኃላ ለቀዋቸዋል።
ከአስር ሰአት በኃላ መምጣታቸው የተነገረው የመጀሊስ ሃላፊዎች በት/ቤቱ ውስጥ ስብሰባ አድርገዋል፡፡
አወልያ ትምህርት ቤት ከአጸደ ህጻናት እስከ 10ኛ ክፍል የዲኑንና ቀለም ት/ት ጎን ለጎን በመስጠት ላይ የሚገኝ ነው፡፡
አወልያን ትምህርት ቤቱን ለማቋቋም የአካባቢው ሙስሊሞች በደርግ ዘመን ከፍተኛ ትግል ያደረጉ ከመሆኑም በላይ እስከመታሰር የደረሱም ነበሩ፡፡
ት/ት ቤቱ ከዚህ ቀደም በኢራን ፤ ከዚያም በአወሊያ ስር በነበረበት ጊዜ ጥሩ ተማሪዎችን በማፍራትና ለከፍተኛ ደረጃ ከማድረሱ ባሻገር፤ አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች በነጻ ከማስተማር ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡
መጅሊሶች ከመንግስት ጋር በማሴር የአወሊያን አስተዳደር አባረው ከተቆጣጠሩት በኃላ ት/ቤቱ እጅግ እየተዳከመ በመሆኑና ለመምህራን እንኳን በወቅቱ ደሞዛቸውን መክፈል ባለመቻሉ መምህራን ት/ቤቱን እየለቀቁ ሲሄዱ ይታያል፡፡
ትናንት የተካሄደው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ከትናንት በስተያ ሰኞ ዕለት ውንጌት አካባቢ ያለው ዋናው የአወሊያ ግቢ ተማሪዎች ያሰሙትን ተቃውሞ ተከትሎ ነው፡፡
ሙስሊሞች መብታችን ተረግጦ የማንተኛ መሆኑን መንግስት እንዲያውቅ ማስገንዘብ እንፈልጋለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡