(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 11/2009) በ2017 ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ አፍሪካውያን ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ የከፋ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
በርካታ ዜጎች ይፈናቀሉባቸው ተብለው በግንባር ቀደምትነት ከተቀመጡት ሀገራት ተርታም ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች።
አለም አቀፉን የሰብአዊነት ቀን አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ባወጣው መግለጫ የአፍሪካውያን የኑሮ ቀውስ በተያዘው አመት ተባብሶ ቀጥሏል ይላል።
የህዝብ መፈናቀል ከየትኛውም አመት ልቆ መታየቱንም ይፋ አድርጓል።
እንደ መግለጫው ከሆነ በ2017 ብቻ 20 ሚሊየን አፍሪካውያን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ከ44 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ተፈናቃዮችም ከጉዟቸው ተያይዞ ለከፋ የምግብ እጥረት ተዳርገዋል።
በአለም አቀፉ የሰብአዊነት ቀን ዋዜማ የወጣው የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት በስደተኝነት ከሚመዘገቡትና ጥገኝነት ከሚጠይቁት በላይ የውስጥ መፈናቀልም የከፋ እንደሆነ አመላክቷል።
በ2017 ብቻ በሀገራቸው ውስጥ የተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥር 12 ነጥብ 7 ሚሊየን ደርሷል።
ይህ አሃዝ በ2013 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ65 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ከ51 በላይ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ሰራተኞች እንደተገደሉ ያመለከተው ሪፖርት በተለይም በማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣በሶማሊያ፣በኬንያና በደቡብ ሱዳን በሰብአዊ መብት ሰራተኞች ላይ የሚደርሰው የሞት አደጋ የከፋ መሆኑን አስታውቋል።
ይህ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት በከፍተኛ ሁኔታ ህዝብ ይፈናቀልባቸዋል ያላቸውን አስር የአፍሪካ ሀገራትን ስም ዝርዝርም ይፋ አድርጓል።
በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን ሲያስቀምጥ ኢትዮጵያን በ9ኛ ደረጃ ላይ ፈርጇታል።
በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰተው ድርቅና ረሃብ፣ በየአካባቢው ባለው የድንበርና የጎሳ ግጭት እንዲሁም በመንግስት በሚመራው የመሬት ቅርምትና ነጠቃ ምክንያት በየአመቱ በ100ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደሚፈናቀሉ መዘገቡ የሚታወስ ነው።