ኢሳት ( መጋቢት 29 ፥ 2008)
በተያዘው የፈረንጆች አመት (2016) ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በኢትዮጵያ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጠ።
ድርቁ እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ የጎርፍ አደጋም ለሰዎቹ መፈናቀል ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ድርጅቱ በወቅታዊው የኢትዮጵያ የድርቅ ሁኔታ ዙሪያ በወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
አሁን በሃገሪቱ ተከስቶ ካለው የድርቅ አደጋ አንጻርም በቂ የህክምና አገልግሎቶች ተሟልተው አለመገኘታቸውን የገለጸው ድርጅቱ በድርቁና በጎርፍ አደጋ የሚከሰተው ጥፋትም የበርካታ ሰዎችን ህይወት ሊቀጥፍ እንደሚችልም አሳስቧል።
በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎችም የወባ በሽታን ጨምሮ ህጻናትን በአጣዳፊ የሚገድሉ ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ ሊከሰቱ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ ገልጿል።
በድርቁ ሳቢያ በተፈጠረው የምግብ ኣጥረት ክፉኛ የአካልና የጤና ጉዳት ደርሶባቸው የሚገኙ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ህጻናትም እየተባባሰ በሚሄደው የድርቅ አደጋ ያልተጠበቀ አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
ወደ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ የሚደርሱና በምግብ እጥረት ላይ የሚገኙ እርጉዝ እናቶችም በምግብ እጥረቱ ምክንያት እርግናቸው ሊጨናገፍ እንደሚችል ድርጅቱ አሳስቧል።
ለተረጂዎች የሚደርስ የእህል እርዳታ በጅቡቲ ወደብ ቢደርስም በወደቡ የተፈጠረ መጨናነቅ የእርዳታ እህሉ ለተረጂዎች በወቅቱ እንዳይደርስ ታውቋል።
የጫኑትን የእህል አቅርቦት ማውረድ ያልቻሉ ከ10 በላይ መርከቦችም ወደሱዳንና ሶማሊላንድ በርበራ ወደብ እያቀኑ መሆናቸውን የመንግስት ባለስልጣናት መግለጻቸው ይታወሳል።
ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከተጋለጡት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከልም 3.6 ሚሊዮን የሚሆኑት የህክምና ድጋፍን የሚፈልጉ እንደሆነ ታውቋል።
በስድስት ክልሎች ተከትስቶ ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ ወደ ረሃብ ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ የሚባሉ ወረዳዎች ቁጥርም ኣየጨመረ መምጣቱን የእርዳታ ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው።
ሰሞኑን በጅጅጋ ከተማ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ50 የሚበጡ ደግሞ የገቡበት አለመታወቁ መገለጹም ይታወሳል።