ህዳር ፳፯(ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅድመ መደበኛ ት/ቤት ገብተው መማር ከሚገባቸው እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ሀፃናት ውስጥ 23 በመቶዎቹ ወደ ትምህርት ቤት አለመምጣታቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው ሰነድ ያስረዳል። ከ1ኛ አስከ 4ኛ ክፍል ድረስ የትምህርት ገበታቸው ላይ የተገኙ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የሚያሳያየው ሰነዱ፣ከ5ኛ አስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ገብተው መማር የነበረባቸው ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑንም ያመለክታል ፡፡
በዚህ ዓመት መድረስ የነበረበት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቅበላ 52.7 ቢሆንም የተሳካው 38 በመቶ ብቻ ነው ።
በ2005 ዓ/ም የት/ም ሂደቶች ሁሉ አሳሳቢ የነበረው የሚያቋርጡ ተማሪዎች መብዛት መሆኑን ያስታወሰው ሰነዱ፣ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ለመማር ተመዝግበው ያቋረጡ ተማሪዎች እስከ ሰባት ሚልየን ይደርሳሉ ብሎአል።
አራት ሚሊየን የሚሆኑ የኢትዮጵያ ህፃናት ጭራሽ ትምህርት ቤት አለመግባታቸውም ተጠቅሷል። አሁን ባለው መረጃ መሰረት 22 ሚሊየን ህፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ ፡፡
በሁለተኛ ደረጃ እና በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሉ ታዳጊ ወጣቶች ተመዝገበው ትምህርታቸውን መከተታል ከጀመሩ በሁዋላ ከሁለት ሚልየን በላይ ተማሪዎች ከትምህር ገበታቸው ቀርተዋል፡፡
እያንዳንዱ የትምህር አይነትና ዋና ዋና ፈተናዎች የተማሪዎች ውጤት ደረጃ ሲገመገም መሻሻል ቢኖረውም ይደረስበታል በተባለው ልክ አለመደረሱ ተጠቅሷል።፡
ቁርሳቸውን በልተው ለመማር መቸገራቸው፤ ትምህርትን በፍራቻ ማየት፤ ካለው የኢኮኖሚ ድቀት የተነሳ ልጆች እየሰሩ ሆዳቸውን እንዲሸፍኑ መገደዳቸው ለማቋረጣቸው በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
በየቀኑ በርሃብ ምክንያት አዙሮቸው ሚወድቁ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱም ተመልክቷል፡፡
ይህ ሪፖርት ለኢህአዴግ ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።