በ2005 ዓም ኢትዮጵያ ከወደቁ አገራት ምድብ ተመደበች

ሰኔ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-ፎሬን ፖሊሲ መጽሄት በእያመቱ በሚያወጣው የወደቁ አገራት ሪፖርት ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር ፌልድ ስቴትስ ኢንዴክስ ኢትዮጵያ እንደ አለፉት አመታት ሁሉ ዘንድሮው የወደቁ ወይም በመውደቅ ላይ ካሉ 20 አገራት መካከል አንዷ ሆና ተመድባለች። የህዝብ ቁጥር ፣ የስደተኛ ቁጥር፣ የህዝብ ብሶት፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ያልተመጣጠነ እድገት፣ የመንግስት ህጋዊነት፣ ማህበራዊ አገልግሎት፣ የደህንነት ጥበቃ፣ የሊህቃን መከፋፈልና የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚሉት መስፈርቶች ተገምግዋል።

በዚህም መሰረት ከ1 እስከ 20 ያሉት አገራት ህልውናቸው  አስተማማኝ ያልሆነ ከፍተኛ ችግር ያለባቸው ተብለው ተመድበዋል። ሶማሊያ ቀዳሚ የወደቀች አገር ስትባል፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ሱዳን፣  ደቡብ ሱዳን፣ ቻድ፣ የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ሀይቲ ፣ ሴንትራል አፍሪካ ፣ ዝምባብዌ፣ ኢራቅ ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ፓኪስታን፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ኬንያ፣ ኒጀር፣ ኢትዮጵያና ቡሩንዲ ተከታታዮችን ደረጃዎች ይዘዋል።

ከሀያዎቹ አገራት የተሻሉ ተብለው በሁለተኛው ምድብ ውስጥ ከሚገኙት መካከል ደግሞ ሶሪያ፣ ዩጋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኤርትራ፣ ማይናማር፣ ካሜሩን፣ ስሪ ላንካ፣ ባንግሊያዲሽ፣ ኔፓል፣ ሞሪታኒያ፣ ኢስት ቲሞር፣ ሴራ ሊዮን፣ ግብጽ ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኮንጎ፣ ኢራን፣ ማሊ፣ ርዋንዳ እና  ማላዊ ተመድበዋል።

 

የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያ በተሻለ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የደህንነት ጥንካሬ ላይ እንደምትገኝ በተደጋጋሚ ሲናገር ይሰማል። ይሁን እንጅ የፎሬን ፖሊስ መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ  ባለፉት ተከታታይ አመታት ይህ ነው የሚባል የደረጃ መሻሻል አልታየባትም። በዚህ አመትም ኤርትራ በአንጻራዊ መልኩ ከኢትዮጵያ በተሻለ ደህንነት ላይ እንደምትገኝ ሪፖርቱ ሲያሳይ፣ ኬንያ፣ ናይጀሪያና ሱዳን ደግሞ ከኢትዮጵያ አንሰው ተገኝተዋል።