(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 8/2009)በእንግሊዝ ለንደን በተካሄደው 16ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ የ7ኝነት ደረጃን አገኘች።
ከአፍሪካ ደግሞ የ3ኝነት ደረጃን ይዛለች።
ኢትዮጵያ እነዚህን ደረጃዎች የያዛቸው ሁለት የወርቅና ሶስት የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት ነው።
ቅዳሜ ምሽት በተካሄደው የወንዶች 5ሺ ሜትር ውድድር አትሌት ሙክታር እድሪስ ሞፋራህን በማሸነፍ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ ማስገኘቱ ታውቋል።
በ5ሺ ሜትር ሴቶች በ10 ሺ ሜትር ርቀት ወርቅ ያስገኘችው አልማዝ አያና ሁለተኛ በመውጣትና የብር ሜዳሊያ በማግኘት ለሀገሯ ሁለት ሜዳሊያዎችን አበርክታለች።
ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በ10 ሺ ሜትር 2ኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ማስገኘቷ አይዘነጋም።
በወንዶች ማራቶን አትሌት ታምራት ቶላ በውድድሩ ሁለተኛ በመውጣት ለሀገሩ በሻምፒዮናው የብር ሜዳሊያ ማስገኘቱ ይታወሳል።
እሁድ ምሽት በተጠናቀቀው 16ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሜሪካ በ10 የወርቅ፣በ11 የብርና በ9 የነሀስ ሜዳሊያዎች ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቃለች።
ኬንያ ደግሞ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ስትሆን ደቡብ አፍሪካ በ6 ሜዳሊያዎች የ3ኝነት ደረጃን ይዛለች።
ኢትዮጵያ ደግሞ ሁለት የወርቅና ሶስት የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሻምፒዮናውን በ7ኝነት ደረጃ ስታጠናቅቅ ከአፍሪካ ደግሞ የ3ኝነት ደረጃን ይዛለች።
በ16ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 43 ሀገራት በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባታቸውን ዘገባው አመልክቷል።