በፖታሽ ማዕድን ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራ የእስራዔል ኩባንያ ፕሮጄክቱን መዝጋቱን አስታወቀ

መስከረም 26 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ በፖታሽ የማዕድን ኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ አንድ የእስራዔል ኩባንያ የኢትዮጵያ መንግስት የገባውን ቃል ተግባራዊ አላደረገም በማለት ፕሮጄክቱን ለመዝጋት ወሰነ።

ኩባንያው የደረሰውን ውሳኔ ተከትሎ ለፕሮጄክቱ የመደበው 179 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ እንዳይንቀሳቀስ ሲል ነው ዮርክ ከተማ ለሚገኘው የአለም አቀፉ የንግድ ልውውጥ ማዕከል ማስታወቁን ግሎብስ የተሰኘ የእስራዔል የቢዝነስ መጽሄት ሃሙስ ዘግቧል።

ILC የሚል መጠሪያ ያለው ኩባንያው የኢትዮጵያ መንግስት ፕሮጄክቱን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲረዳ ቃል ገብቶ የነበረውን የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዳላከናወነ ቅሬታውን አቅርቧል።

ይኸው የእስራዔል ኩባንያ ከወራት በፊት በአፋር ክልል የሚገኘውን የአላን የፖታሽ ማዕድን ልማት ለማካሄድ 109 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ የባለቤትነት ድርሻ መረከቡ ታውቋል።

ይሁንና የማዕድን ኩባንያው ከተለያዩ ችግሮች ሊያካሄድ ያቀደውን ስራ ተግባራዊ ማድረግ እንዳልቻለ ቅሬታውን አቅርቧል።

ILC የተሰኘው ይኸው ኩባንያ በኢትዮጵያ መንግስት የታክስ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ከግብር ክፍያ ጋር በተያያዘ ያቅረበው አቤቱታ ተቀባይነት አለማግኘቱ ቅሬታ እንዳሳደረበትም አክሎ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የእስራዔሉ ድርጅት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እዳ አለበት ሲል ከወራት በፊት ክፍያ እንዲፈጸም ቢጠይቀውም ድርጅቱ ክፍያን በመቃወም ትዕዛዙን አለመፈጸሙ ታውቋል።

በሁለቱ ወገኖች መካክል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎም ኩባንያው ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጠቅልሎ ለመውጣት የወሰነ ሲሆን፣ ለፕሮጄክቱ ተግባራዊነት የመደበው ከ3 ቢሊዮን ብር በላይም እንዳይንቀሳቀስ አድርጓል።

ባለፈው አመት የተባባሩት አረብ ኤመሬቶች አንድ ኩባንያ ተመሳሳይ ቅሬታን በማቅረብ በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ስራ ማቋረጡ ይታወሳል። የእስራዔሉ ኩባንያ በፖታሽ ኢንቨስትመንት ላይ በሃገሪቱ ለመሰማራት በማሰብ ከፍተኛ ገንዘብ ሲመደብ የመጀመሪያ እንደሆነ መመረዳት ተችሏል።

የእስራዔሉ ኩባንያ ከወሰደው ዕርምጃ በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን ድረስ የተሰጠ ምላሽ የለም።

በኢትዮጵያ በአዲስ መልክ በኦሮሚያ ክልል በመዛመት ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የእስራዔል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎች በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲወስዱ ረቡዕ ማሳሰቡ ይታወሳል።