ኢሳት (ጥር 2 ፥ 2009)
መንግስት ጉዳያቸው በፖሊስ ምርመራ ላይ የሚገኙትን ዶ/ር መረራ ጉዲና በነጻ የማሰናበት ፍላጎት እንደሌለው ገለጸ።
በወቅታዊ የሃገሪቱ አበይት ጉዳዮች ዙሪያ ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መግለጫን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ዶ/ር መረራ እንደማይለቀቁ መናገራቸውን ለአሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሩ ይልቁኑ ለፍትህ ይቀርባሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በቅርቡ ከአውሮፓ የፓርላማ አባላት ጋር ለመወያየት ወደ ቤልጅየም ተጉዘው የነበሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና በቆይታቸው ከአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር ጋር ተገናኝተዋል ተብለው ከጉዞ ሲመለሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚቆጣጠረው ኮማንድ ፖስት ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።
የኦፌኮ አመራሩ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፖሊስ የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ለመመስረት የሚያስችለውን ምርመራ እያካሄደ መሆኑን በመግለጽ ሰሞኑን ለሁለተኛ ጊዜ የ22 ቀን የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ፈቃድ ተሰጥቶታል።
መንግስት በምርመራ ላይ የሚገኙትን ዶ/ር መረራ ጉዲና የመልቀቅ እቅድ ይኑረው እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ሃይለማሪያም፣ መንግስት የመልቀቅ ፍላጎት እንደሌለውና ይልቁኑ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ ፍላጎት መኖሩን ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል።
የአውሮፓ ፓርላማ እና የአውሮፓ ህብረት መንግስት ዶ/ር መረራ ጉዲናን ለእስር የዳረገበትን ዕርምጃ በይፋ ግልጽ እንዲያደርግ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊነት በመቆጣጠር ላይ የሚገኘው ኮማንድ ፖስት ዶ/ር መረራ አዋጁን ጥሰው በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸውን ገልጿል።
በኦፌኮ አመራር ላይ ምርመራን እያካሄደ የሚገኘው ፖሊስ በበኩሉ ዶ/ር መረራ ላይ የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ለመመስረት የሚያስችለውን እያካሄደ መሆኑን በቅርቡ ለፍርድ ቤት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሩን ለእስር መዳረጉ አሳስቧቸው እንደሚገኝ በመግለጽ ላይ ናቸው።
በጥቅምት ወር ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ከ22 ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል። አዋጁ መቼ እንደሚነሳ የተጠየቁት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አዋጁ ከመነሳቱ በፊት የተገኙ ውጤቶች መታየት ይኖርባቸዋል ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።