በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ በትግራይ አርሶ አደሮች ሰብሎቻቸውን የመስኖ ውሃ እንዳያጠጡ መከልከላቸውን ተናገሩ

የካቲት ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ በሩባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮች ለኢሳት እንደገለጹት፣ የአረና ፓርቲ አባላት ናቸው በሚል የመሰኖ ውሃ እንዳያጠጡ በመከልከላቸው፣ ሰብሎቻቸው እየደረቁ ነው።

12 አርሶ አደሮችን በመወከል ለኢሳት የተናገረው አቶ ህድሮም ሃይለስላሴ የተቃዋሚ አባላት ብቻ በመሆናችን አትክልቶቻችንን የመስኖ ውሃ እንዳያጠጡ፣ ከእነሱ መካከል ሁለቱ ብቻ የተቃዋሚ አባላት ቢሆኑም፣ ዘመዶቻቸው ሁሉ ተክሎቹን ውሃ እንዳያጠጡ እንደተከለከሉ ተናግረዋል። ከፓርቲው ከወጣችሁ ውሃ የማጠጣር ፈቃድ ታገኛላችሁ መባላቸውን የሚናገሩት አቶ ህድሮም፣ በአቋማቸው በመጽናታቸውና ፈቃድ በመከልከላቸው በተለይ ቋሚ ተክሎች እየጠወለጉ መሆኑን  አክለዋል

ህወሃት 40ኛ አመቱን ሲያከብር ለክልሉ ልማትና ዲሞክራሲን ማምጣቱን ተናግሯል፣ እርስዎ ደግሞ ችግር አለ ይላሉ ተብለው የተጠየቁት አቶ ህድሮም፣ ህወሃት በደርግ ጊዜ የተቀበሩ አስከሬኖችን ሲያወጣ ፣ አሁን ያለውን ህዝብ ግን በቁሙ እየቀበረው ነው የሚል መልስ ሰጥተዋል። የትግራይ አርሶአደር በማዳበሪያ እና በሌሎችም እዳዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝና የቻለው ወደ አረብ አገር እየተሰደደ መሆኑን አክለዋል።

በተመሳሳይ ዜናም በትግራይ ከፍተኛ የዘይት እጥረት መፈጠሩንና ህዝቡ ዘይት ለማግኘት ረጅም ሰልፎችን መጠበቅ ግድ እንደሚለው መረጃዎች አመልክተዋል።