በፓሪስ ሶስት የኩርድ አማጽያን አባላት ተገደሉ::

ጥር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ግድያው የተፈጸመው ሀሙስ ጧት ሲሆን ሶስቱም ግንባራቸው ላይ በጥይት ተመትተዋል። ከማቾቹ መካከል አንደኛዋ የኩርድ የሰራተኞች ፓርቲ መስራች ናቸው።

ሳኪና ካንዚስ የተባለችዋ ሟች ፒኬኬ በአውሮፓ ውስጥ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ቁልፍ ሰው እንደነበረች ዘገባዎች ያመለክታሉ።

በሶስቱ ሴት ታጋዮች ላይ የተፈጸመው ግድያ የቱርክ መንግስት በእስር ላይ ከሚገኘው የፒኬኬ መሪ አብደላ ኦቻላን ጋር ንግግር በጀመረ ማግስት ነው።

ብዙ ኩርዶች ግድያውን አስፈጸመው የቱርክ መንግስት ነው በማለት ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡ የቱርክ መንግስት በበኩሉ የኩርድ አማጽያን እርስ በርሳቸው መገዳደላቸውን ይገልጻል።

ፒኬኬ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኩርዶችን በማሰባሰብ ነጻ የኩርዶች አገር ለመመስረት የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው። አብዛኞቹ የምእራብ አገሮች ድርጅቱን በአሸባሪነት ቢፈርጁትም በአባላቱ ላይ እርምጃ ሲወስዱ አይታዩም።