በፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ተመጣጣኝ ልማት ለማረጋገጥ የተዘጋጀ እቅድ አልተሳካም የሚል ሪፖርት ለአዲሱ ሚንስትር ካሳ ተ/ብርሐን ቀረበላቸው፡፡

ኀዳር ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አዲሱ ሚንስትር በአዲሱ የስልጣን ወንበራቸው ተገኝተው ከሚንስትሩ መስሪያቤት ሰራተኞች ጋር ባደረጉት ትውውቅ ያለፉትን አምስት አመታት ሂደት በመገምገም እና የሰራተኛውን የመልካም አሰተዳደር ችግር እንዲያቀርቡ በውይይት ስራ ጀምረዋል፡፡
ሰራተኞች በግልፅ የሚንስትር መስሪያ ቤቱ ክንዋኔዎች እንዲገመግሙ እና ስሀተት ካለ ታርሞ እንዲቀጥል በሰጡት እድል በሚኒስቴሩ የተመጣጣኝ ልማት የማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ያስበነውን ግብ መምታት አልቻልንም ሲሉ አስቀምጠዋል፡፡
ይህም በፌዴራል የልዩ ድጋፍ ቦርድና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ዓመታዊ ግምገማ የጋራ መድረኮች የተገመገመና የጋራ መግባባት የተደረሰበትና ያረጋገጠው ቢሆንም ይፋ ከመሆን ግን ታግዷል ብለዋል፡፡
በዕድገት አቅጣጫዎች መሰረት በአፋርና ሶማሌ ክልሎች ባለፉት አምስት አመታት በቂ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ ባሉባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ነዋሪዎች 2/3ኛውን የአፋርና ሶማሌ ክልል ሕዝብ በተመረጡ የልማት ማዕከላት በማሰባባሰብና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ የሕዝቡን የአኗኗር ዘይቤ ከመሠረቱ ለመለወጥ የተኬደበት መንገድ ግቡን አልመታም ሲሉ ባለስልጣኑ አክለዋል፡፡
ባለፉት አምስት አመታት በቂ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ በሌሉባቸው ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ከሚገኙ ነዋሪዎች 25 በመቶ በአፋር እና በሱማሌ አባወራዎች እና እማወራዎች የድርቅ ተጋላጭነታቸውን የሚቀንሱ ፕሮጀክቶችን በመተግበርና ተንቀሳቃሽ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ የተኬደበት መስመር ግቡን መምታት ባለመቻሉ አሁን ለተከሰተው ርሐብ እንደማሳያ ሁኖ ማለፉም በውይይቱ ተነስቷል።
የመንደር ማሰባሰብ ስራ ለመስራት ታቅዶ እስኩን በጋምቤላ 17 በመቶ፣ በሶማሌ 28 በመቶ፣ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 16 በመቶ ብቻ መከናወኑ በውይይቱ ተገልጾ፣ ለማሰባሰቡ እንደ ምክንያት ከቀረቡት መካከል የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት፤የመብራት እና ስልክ አቅርቦት አለመሟላት እንዲሁም ባለፉት ሶስት አመታት ሙሲሊሙ ከፖለቲካ ስርዓቱ በፈጠረው አለምግባባት ችግሩን በተቀናጀ ግብረሐይል ለመምራት ወጭዎችን አክራሪነት እና ፅንፈኝነትን ለመዋጋት በማዋላችን ነው ሲሉ ዳይሬክተር ጄኔራሉ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩን ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም በአግባቡ አልመርቱም አሰተዳደራዊ በደል ደርሶብናል ያሉ አሰተያየት ሰጭዎች በእድገት እና ደሞዝ ጭማሪ ላይ ጥያቂያቸውን አቅርበዋል።