ኢሳት (ሃምሌ 19 ፥ 2008)
በሰሜን ፈረንሳይ አገር በካላይስ የወደብ ከተማ በስደተኞች መካከል ግጭት ተከስቶ አንድ ኢትዮጵያዊ መገደሉ ተነገረ። ሌሎች ስድስት ስደተኞች መቁሰላቸውም ለማወቅ ተችሏል።
ዛሬ ማክሰኞ በተቀሰቀሰው በዚህ ግጭት ከሱዳን፣ ኤርትራና፣ ኢትዮጵያ ወደ ፈረንሳይ የገቡ ስደተኞች ከአፍጋኒስታን ከመጡ ሌሎች ስደተኞች ጋር ተጋጭተው በጩቤ እንደተወጋጉና እንዲሁም በዱላ እንደተደባደቡ አር ኤፍ አይ (RFI) የተባለ የፈረንሳይ የዜና አውታር የአካባቢው ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ስሙ ያልተገለጸው የ37 ዓመት እድሜ ያለው ኢትዮጵያዊ በጩቤ ደረቱ ላይ ተወግቶ እንደሞተ የዜና አውታር በድረገጹ ላይ ባወጣው ዘገባ አስታውቋል። የፈረንሳይ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት በስደተኞች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር ጣልቃ እየገባ ሲከላከል እንደነበር RFI በዘገባው አክሎ አስረድቷል።
በዚሁ ፈረንሳይ አካባቢ ወደ እንግሊዝ አገር ለመግባት የሚፈልጉ ብዛት ያላቸው ስደተኞች ይኖራሉ ተብሏል።
ከዚህ ቀደም እኤአ ግንቦት 26 ፥ 2016 በሰደተኞቹ መካከል ግጭት ተቀስቅሶ 40 ሱዳናውያን መቁሰላቸውን የዜና ወኪሉ በዘገባው አስታውሷል።
በካላይስ ወደብ አካባቢ 7,000 ከተለያዩ አገር የመጡ ስደተኞች እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፣ በዚሁ አመት በካላይስ ስደተኞች መጠለያ በስደተኞች መካከል በተከሰተ ግጭት እስካሁን ድረስ 8 ስደተኞች ሲሞቱ፣ ብዛት ያላቸው መቁሰላቸውን አር ኤፍ አይ (RFI) ዘግቧል።
ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳንና ከኤርትራ የፈለሱ ስደተኞችን በእቃ መጫኛ ተሽከርካሪ በመሆነ ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ እንደሚገቡ በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ ከሁለት ወር በፊት የእንግሊዝ ፖሊስ ብዛት ያላቸው ሱዳን፣ ኤርትራና የኢትዮጵያ የፈለሱ ስደተኞችን ፖርስትማውዝ በተባለ ቦታ መያዙን መዘገባችን ይታወሳል።
እንግሊዝ በቅርቡ ከአውሮፓ ህብረት የተለየችበት ዋነኛው ምክንያትም ይኸው የስደተኞች ጉዳይ እንደሆነ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ቢቆዩም፣ የእንግሊዝ መንግስት ከአውሮፓ ህብረት አባላት በተለይም ከፈረንሳይ፣ ቤልጅየምና፣ ሆላንድ ጋር በመተባበር የሰው አዘዋዋሪ መረብ ለመበጣጠስ፣ ህወገጥ ፍልሰትን ለማስቆም እየሰራ እንደሆነ ገልጿል።