የካቲት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኤጄንሲው ኃላፊ ጋይለ ስሚዝ ይህን ያሉት ሀሙስ እለት የኢትዮጵያን ረሀብና መሰጠት ያለበትን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስመልክተው ለአሜሪካ የአደጋ ጊዜ ደራሽ ቡድን በሰጡት መግለጫ ነው።
እንደ ሲ ኤን ኤን ዘገባ በድርቅ ምክንያት የሚከሰተውን የደህንነት ስጋት ማስወገድ እንዲቻል የኦባማ አስተዳደር በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን የከፋ ድርቅ የሚቃኝ፣ የሚያስፈልገውን አስቸኳይ የእርዳታ መጠን የሚያሳውቅና ድጋፍ የሚያደርግ የአደጋ ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ ቡድን ወደ ስፍራው ልኳል።
እንደ ኤክስፐርቶች ገለጻ ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ባለፉት ትውልዶች ሁሉ ያልታዬና እጅግ የከፋ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1984 ማለትም በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1977 የተከሰተው ድርቅ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን በመግደሉ እንደ ማይክል ጃክሰን፣ ስቲቭ ዎንደር እና ብሩስ የመሣሰሉ የዓለማችን ታላላቅ አርቲስቶች በመሰባሰብ “ዊ አር ዘ ወርልድ” የተሰኘ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ሙዚቃ መልቀቃቸውን ሲ ኤን ኤን አስታውሷል።
ሲ ኤን ኤን አክሎም በጸረ ሽብርተኝነት ትግሉ ዙሪያ የዩናይትድስቲትስ ዋነኛ አጋር የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆን ህዝቡ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ግምቱን አስቀምጧል ይላል።
ከነዚህ መካከል 8 ሚሊዮን ያህሉ በቋፍ ላይ ያሉና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆኑ፤ 2 ሚሊዮን ያህሉ ንጹህ የመጠጥ ውሀ የሌላቸው ናቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ቢልም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግን በኢትዮጵ በአስከፊ የምግብ እጥረት ላይ የሚገኙ ሰዎች ከ15 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆኑ መገመቱንና በስፋት እርዳታ ካልተገኘ ሁኔታ እጅግ አስከፊ እንደሚሆን ማስጠንቀቁን ሲ.ኤን ኤን ጠቅሷል።
በቅርቡ የአሜሪካ ዓለማቀፍ የልማት ኤጀንሲ ሆነው በኦባማ ሲሾሙ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በገዥው ፓርቲ ደጋፊነት ወቀሳ የተሰነዘረባቸው ጋይለ ስሚዝ “በማደግ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ከገጠማት የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግ ጥረት እያደረግን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጋይለ ስሚዝ አክለውም ሌሎች ሀገራትም ለኢትዮጵያ እርዳታ እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል።
“እንዲሁም ሌሎች ለጋሾችም አሁኑኑ ምላሻቸውን ሊሰጡ ይገባል” ያሉት ጋይለ ስሚዝ፣ “ ለችግሩ አስቸኳይ ምላሽ መስጠት የሞራል ብቻ ሳይሆን የሀገራዊ ደህንነትም ጉዳይ ነው።” ብለዋል።