ሚያዚያ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፉት ሶስት ቀናት ከቅማንት ህዝብ የማንነት እና የአስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተነሳው ተቃውሞ ዛሬ ጋብ ብሎ የዋለ ቢሆንም፣ መንግስት ያሰራቸውን የብሄረሰቡን ወኪሎችና መምህራኖችን የማይፈታ ከሆነ፣ ነገ ቅዳሜ በድጋሜ ተቃውሞ እንደሚያስነሱ ተማሪዎች አስጠንቅቀዋል።
የወረዳው ባለስልጣናት በበኩላቸው ቀሳውስቱንና አገር ሽማግሌዎችን በመያዝ ከተማሪዎች ጋር ለመነጋገር የሽምግልና ጥረት ጀምረዋል። የልዩ ሃይል የፖሊስ አባላት ዛሬም ድረስ በአይከል ከተማ በመንገድ ላይ ሲዘዋወሩ ያገኟቸውን ወጣቶች ሲደበድቡ መታየታቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ እስር እና ድብደባውን በማምለጥ ከከተማው የወጡ ተማሪዎች፣ ድርጊቱ እንዲቆም፣ የታሰሩ ሰዎችም ባስቸኳይ እንዲፈቱ አሳስበዋል።
ሰዎቹ ካልተፈቱ ተቃውሞው ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚሉት ተማሪዎች፣ ለሚጠፋው የሰው ህይወት ወይም ለሚደርሰው የንብረት መውደም የመንግስት ባለስልጣናት ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።
በከተማዋ አብዛኛው ሱቆች እስከ እቀኩለቀን ድረስ ዝግ ሆነው ውለዋል። የወረዳውን ባለስልጣናት አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።