ግንቦት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከጎንደር ከተማ 55 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በጭልጋ ወረዳ አለምጸሀይ ቀበሌ አመክሊን እየተባለ በሚጠራ ጎጥ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደሮች “ ለ አገር ውስጥ ባለሀብት ሊሰጥ ነው”ከተባለው ይዞታቸው እንዲነሱ የቀረበላቸውን ጥያቄ በመቃወማቸው በታጠቁ የክልል እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት መንደራቸው ተከብቦ ተኩስ እንደተከፈተባቸው የ ኢሳት ወኪል ከስፍራው ዘግቧል።
ይዞታችንን አንለቅም ያሉት ሁሉ ሚያዚያ 29 ቀን 2005 ዓመተምህረት ከፍተኛ ድብደባ ከተፈጸመባቸው በሁዋላ ወደ 60 የሚጠጉት የአካባቢው ነዋሪዎች አይከል በሚገኘው እስር ቤት ታስረዋል።
የ ዓይን እማኞች እንዳረጋገጡት በፖሊሶች በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ዘግኛኝ ጉዳት የደረሰበት ውቤ አዛናው የተባለ የ 7ኛ ክፍል ተማሪ ጎንደር ሆስፒታል ተወስዶ ህክምና እየተከታተለ ይገኛል።
ችግሩ የተፈጠረው የወረዳው አስተዳደር ከነዋሪዎቹ ጋር ሳይነጋገር እና ሳይመካከር በድንገት ይዞታቸውን ሸንሽኖ ለሀገር ውስጥ ባለሀብት ለመስጠት በመነሳቱ ነው።
ነዋሪዎቹ የ አስተዳደሩን ድንገተኛ ጥያቄ በመቃወም “ይዞታችንን አናስነካም” ሲሉ፤ በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ የክልል እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት መንደሩን በመክበብ ተኩስ ከፍተውባቸዋል፣በቆመጥ ደብድበዋቸዋልም።
ከታሰሩት የ አካባቢው ነዋሪዎች መካከል በፖሊስ ድብደባ እጃቸው የተሰበረው ቄስ ተረፈ ጽጌ እና ጭንቅላታቸውን ክፉኛ የተጎዱ ቄስ ተክሌ በላይ ይገኙበታል።
እንዲሁም አቶ ብርሀኑ ዘገዬ፣ አቶ ተገኑ ደገፋ፣ወጣት ደመወዝ አዳነ፣አቶ እያዩ ካሴ፣ወጣት የኔሁን አበራ፣ወጣት አንዳርግ ጌጡ፣አቶ ታደለ ዓለማየሁ፣አቶ አወቀ ቸኮል፣ወጣት ባበይ አቢ፣ተማሪ ሙሉ አጣናው፣ አቶ አማረ ደምሴ፣ወጣት ባበይ አበበ፣ወጣት ዓለምነህ መካሻው፣ዲያቆን ታዲዮስ ተሰማ፣ እና አቶ ባዬ በላይ ይገኙበታል።
የ ኢሳት ወኪል እንዳለው፤የሰፈሩ ነዋሪዎች እስካሁን ድረስ በታጣቂዎች እንደተከበቡ ሲሆኑ በርካቶች ደግሞ አካባቢውን ለቀው ወደ በረሀ ተሰደዋል።
በነዋሪዎቹ ላይ ተኩስ የከፈቱት እና ድብደባ የፈጸሙት ታጣቂዎች በጠላት ላይ ጀብዱ እንደፈፀመ ሰው ሲፎክሩና ሢሳሳቁ መታየታቸውን ያመለከተው ወኪላችን፤በጣም አሳዛኙ ነገር ግን ይህን በማድረጋቸው ቦታውን ይረከባሉ በተባሉት ባለሀብት ተብዬዎች በግ እና በሬ ታርዶላቸው ሲጋበዙ መታየታቸው ነው ብሏል።
በተመሳሳይ ዜናም በመተማ ወረዳ ኮኪት ቀበሌ አካባቢ የሚኖሩ ከ3 ሺ በላይ አርሶደሮች መሬታችንን አሳልፈን አንሰጥም በማለት ተቃውሞ ማስነሳታቸውን የአካባቢው ሰዎች ገልጸዋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንደገለጹት ችግሩ የመሬት ባንክ ከተባለው አሰራር እና ለኢንቨስተር እየተባለ ከሚሰጠው ጋር የተያያዘ ነው።