በጨለንቆ አንዲት ወጣት መገደሏን ተከትሎ ተቃውሞ በመቀስቀሱ መንገድ ተዘጋ

ኢሳት (ሰኔ 14 ፥ 2008)

በምስራቅ ሃረርጌ ጨለንቆ ውስጥ የአንዲት ወጣት መገደልን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ በዛሬው ዕለት መንገድ መዘጋቱን የአይን ምስክሮች ከስፍራው ገለጹ። የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሳብሪና አብደላ የተባለች ወጣት ከመስጊድ ወጥታ ስትሄድ በፖሊሶች መገደሏን በመቃወም በተነሳው ተቃውሞ ፖሊሶች ቀብሩን ለመከፋፈል የሞከሩ ቢሆንም፣ በመጨረሻ የቀብሩ ስርዓት መፈጸሙን መረዳት ተችሏል።

ፖሊሶች የግለሰቦችን ጸብ ለማብረድ በሚል ተኩሱን እንደከፈቱ ለኢሳት ከስፍራው የተናገሩት የአይን ምስክሮች፣ መንገደኛዋ ወጣት ሰለባ መሆንዋን አክለው ገልጸዋል።

ፖሊሶም ለግለሰቦች ጸብ ጥይት ወደ ሰዎች የተኮሱበት ምክንያትም አነጋጋሪ ሆኗል። በጉልት ንግድ ቤተሰቦቿን የምትረዳው የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳብሪና አብደላ ከመስጊድ ስትወጣ በመገደሏ የተቆጡት የአካባቢው ነዋሪዎች በማግስቱ ማክሰኞ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀስቅሰዋል። የህዝቡ እንቅስቃሴ ግድያውን ከመቃወም ባሻገር የፖለቲካ ጥያቄዎችን እያነሳ በመምጣቱ ፖሊሶች የቀብሩን ስነስርዓት እንዳይፈጸምና ይባስ ብለው ሰዎች እንዳይሰባሰቡ ለመከላከል የሞከሩ ቢሆንም በህዝቡ ግፊት የቀብሩ ስነስርዓት ማከስኞ ሰኔ 14 ፥ 2008 ተፈጽሟል።